አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

ከባድ ዝናብ የወቅቱ ግብርና ፈተና

በምሕረት ሞገስና በሻሂዳ ሁሴን

ከ2009 ዓ.ም. ማብቂያ ጀምሮ በአዲስ አበባና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች አብዝቶ የጣለው ዝናብ መንገዶችን በጎርፍ ከማጥለቅለቅ፣ ቤቶችን ሰብሮ ከመግባትና የነዋሪዎችን እንቅስቃሴ ለሰዓታት ከመግታት ባለፈም፣ ሰብሎች ላይ ጉዳት ማድረሱ አልቀረም፡፡

በተለይ በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ የአርሶ አደር እርሻዎችና በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ ሥፍራዎች የሚገኙና በቡቃያ ደረጃ ያሉ ሰብሎች መጠኑ በጨመረው ዝናብ ተጎድተዋል፡፡

ሰሞኑን ከአዲስ አበባ ወደ ሰሜን ሸዋ በነበረን ጉዞም በአንዳንድ እርሻዎች ላይ የነበረ የጤፍ ቡቃያ ቢጫ ሆኖ ዓይተናል፡፡ አንዳንዱ እርሻ ደግሞ ውኃ ተንጣሎበት ነበር፡፡ ከባለሙያዎች ለመረዳት እንደቻልነው የጤፍ ቡቃያ ቢጫ የሆነው ውኃው በዝቶበት በመቃጠሉ ነው፡፡

ወደ ጂማ መስመር ባደረግነው ጉዞም ከወሊሶ ወዲህ የሚገኙ ሰፋፊ የእርሻና የግጦሽ መሬቶች በጎርፍ ተጥለቅልቀው ሐይቅ መምሰላቸውን አስተውለናል፡፡ በተለይም የአበባ እርሻ ካለበት ወደዚህ ያለው የተንጣለለ ሜዳ ሙሉ ለሙሉ በጎርፍ ተውጦ ነበር፡፡

አልፎ አልፎ የሚታዩ ዛፎች ሳይቀሩ ከነቅርንጫፋቸው በጎርፉ ተውጠው ነበር፡፡ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ሳይቀር የሰሩትን የቆርቆሮ አጥር ጥሶ ሰተት ብሎ ገብቷል፡፡ ለወትሮው ለግጦሽ ይሰማሩ የነበሩትን ከብቶች እንኳ አላስጠጋ በማለቱ ከብቶቹ በየመንገዱ ጥግ ተኮልኩለው ነበር፡፡

በአካባቢው የሚለሙ አዝርዕቶች የጎርፉ ሰለባዎች ሆነዋል፡፡ ይህ የአየር ንብረት ለውጡ በምን ያህል መጠን ተፅዕኖ እያሳደረ እንደሚገኝ ዓይነተኛ ማሳያ ይሆናል፡፡ በአንደኛው ወቅት ከፍተኛ ሀሩር በተቃራኒው ደግሞ በሌላ ወቅት ከፍተኛ ቅዝቃዜ ውርጭ፣ በረዶና የጎርፍ አደጋ ማስተናገድ እየተለመደ መጥቷል፡፡ አንዴ በድርቅ አንዴ ደግሞ በጎርፍ የአገሪቱ የምግብ ዋስትና ፈተና እንዲገጥመው ሆኗል፡፡

በአገሪቱ ከመደበኛ በላይ ሲጥል የከረመው ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ በቡቃያ ደረጃ የነበሩ ሰብሎች ከተበላሹባቸው ክልሎች የኦሮሚያ ይጠቀሳል፡፡

በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ከፍተኛ ኤክስፐርት አቶ ተዋበ ጫኔ እንደሚሉት፣ በኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን፣ ሰሜን ሸዋ፣ ምዕራብ ሸዋ፣ ደቡብ ምሥራቅ ሸዋ፣ ምሥራቅ ሸዋና አርሲ ዞን በሚገኙ አንዳንድ ወረዳዎች በ13 ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ የተዘሩ የመኸር ሰብሎች ተጎድተዋል፡፡

እንደ አቶ ተዋበ፣ የተበላሹት ቡቃያዎች ያሉበት መሬት እንዲገለበጥና በምትካቸው ቶሎ የሚበቅሉት ምሥር፣ ሽምብራና ጓያ እንዲዘሩ ምክር ተሰጥቷል፡፡ በየደረጃው ያሉ የግብርና ባለሙያዎችም እንዲያውቁት ተደርጓል፡፡

ከባድ ዝናብ የሚቀጥል ከሆነ ውኃው የሚፋሰስበትን መንገድ እንዲተገብሩ፣ እርጥበት መቋቋም የማይችሉ ሰብሎችን ከመዝራት እንዲያዘገዩም ተነግሯል፡፡

ለአደጋው ተጋላጭ ከሆኑ የአገሪቱ ክፍሎች አንዱ በሆነው ሰሜን ሸዋ ዞን ከ3,000 ሔክታር በላይ የሚሸፍኑ ሰብሎች ከወቅቱ ጋር ተያያዥ በሆኑ አደጋዎች ጠፍተዋል፡፡ 2,907 ሔክታር ሰብል በበረዶ፣ 77 ሔክታር በጎርፍ፣ 51.75 ሔክታር በመሬት መንሸራተት፣ 59 ሔክታር በዝናብ ብዛት ጠፍቷል፡፡

በዞኑ የሰብል ልማትና ጥበቃ ቴክኖሎጂ ማስፋፊያ የሥራ ሒደት አስተባባሪው አቶ አበበ ጌታቸው እንደሚሉት፣ ባቄላ፣ አተር፣ ማሽላ፣ ምሥርና 26 ሔክታር ጤፍ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ በመሆኑም 217.3 ሔክታር መሬት የተገለበጠ ሲሆን፣ በ110 ሔክታር ላይ ፈጥነው በሚደርሱ እንደ ጓያና ሽምብራ ባሉ ምርቶች እንዲሸፈን ተደርጓል፡፡ ቀሪው 107 ሔክታር ግን በተለያዩ ምክንያቶች በሰብል ሳይሸፈን ቀርቷል፡፡

አጋጣሚው 3,986 አርሶ አደሮችን ተጎጂ ያደረገ ነው፡፡ ውርጭ ሊከሰት ይችላል የሚል ሥጋት እንዳለ የሚናገሩት አቶ አበበ፣ የተጎጂዎች ቁጥር ከዚህ ሊጨምር እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

ከ11 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ከዞኑ ባለፈው ዓመት መሰብሰብ የተቻለ ሲሆን፣ በዚህኛው ዓመት ደግሞ 16,868,281 ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል፡፡ በአደጋው የጠፋው የምርት መጠን በዕቅዱ ላይ ምን ያህል ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ገና አለመታወቁን ተናግረዋል፡፡

 የዝናቡ መጠን ከመስከረም መግቢያ ይልቅ መውጫው ላይ የቀነሰ ቢሆንም፣ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ መውጣት ከነበረበት ጊዜ እንደሚዘገይ የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ይገልጻል፡፡

የኤጀንሲው የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አህመዲን አብዱልከሪም እንደሚሉት፣ ሰሜንና ሰሜን ምሥራቅ እንዲሁም በምሥራቅ የኢትዮጵያ ክፍል ከዚህ በኋላ የዝናቡ መብዛት ሥጋት አይሆንም፡፡ አልፎ አልፎ ግን ከአምስት እስከ አሥር ሚሊ ሊትር ዝናብ ይጠበቃል፡፡ ይህም ዝናቡ ከአካባቢው እየወጣ መሆኑን ያሳያል፡፡

በምዕራብ የኢትዮጵያ ክፍሎች በሚገኙት ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝና ኢሉአባቦራ ዝናቡ ከጥቅምት የመጀመርያው ሳምንት በኋላ የሚወጣ ሲሆን፣ ዝናቡም ወደ ደቡብ ይሄዳል፡፡

ለደቡብ ሁለተኛ የዝናብ ወቅት ስለሆነ ዝናብ የሚያገኙ መሆኑ ለግጦሽና ለውኃ አቅርቦት ፋይዳው የጎላ ነው፡፡ አልፎ አልፎ የሚኖረው ዝናብ ግን በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት ስለሚያደርስ፣ አርሶ አደሩ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አቶ አህመዲን መክረዋል፡፡  

ዝናቡ ከሰሜንና ሰሜን ምሥራቅ የአገሪቱ ክፍሎች ወጥቶ ወደ ምዕራቡና ደቡብ የአገሪቱ ክፍሎች እስከ መስከረም 30 ቀን 2010 ዓ.ም. የሚሄድ ቢሆንም፣ ትንሽ የመራዘም ሁኔታ ሊኖር ይችላል፡፡ ምክንያቱም አትላንቲክ ውቅያኖስና የደቡብ ህንድ ውቅያኖስ ቅዝቃዜ እየጨመረ ሲሆን፣ ይህም ወደ ኢትዮጵያ የሚገባውን እርጥበት ያበዛዋል፡፡ በዚህም ዝናቡ ለተወሰነ ጊዜ ሊቆይ ይችላል፡፡ በመደበኛ ሁኔታ ሲጥል የነበረው ዝናብም መቆም የነበረበት መስከረም 10 አካባቢ ነበር፡፡

ሆኖም ዝናቡ በመዘግየቱ ከፍተኛ ዝናብ የሚያገኙ አካባቢዎች ቡቃያው በዝናብ እንዳይቃጠል ውኃው የሚወጣበትን (የሚንጠፈጠፍበትን) ዘዴ እንዲተገብሩ፣ የደረሰ ሰብል ካለም ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መክረዋል፡፡ ከባድ ዝናብ የሚያስከትለው ጎርፍ በተደጋጋሚ አገሪቱን እየጎበኛት ይገኛል፡፡ በዚህ ክረምት በአዲስ አበባ ብቻ ሦስት ጊዜ ያህል የጎርፍ አደጋ ተከስቷል፡፡ ንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ አቃቂና ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተሞች የጎርፍ አደጋ አስተናግደዋል፡፡ በሰው ሕይወት የደረሰ አደጋ ስለመኖሩ ባይገለጽም ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ አሉ፡፡

በዝናባማው የክረምት ወቅት የጎርፍ አደጋ የሚጠበቅ ቢሆንም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ድግግሞሹ ከሌላው ጊዜ በተለየ እየጨመረ ስለመምጣቱ ጥርጥር የለውም፡፡ ከየት መጣ ሳይባል ድንገት ዶፍ የመጣሉ ነገር እየተለመደ መጥቷል፡፡

 የጎርፍ አደጋ ሰብሎችን እንዳልነበሩ አድርጎ ከማጥፋት፣ ሰዎችን ከቤት ንብረታቸው ከማፈናቀል ባለፈ ለተለያዩ ውኃ ወለድ በሽታዎች መስፋፋትም ምክንያት ይሆናል፡፡