አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

የወተት ፋብሪካዎችና አቅራቢዎችን የሚገዛ መመርያ ሊተገበር ነው

 

የአገሪቱ የወተት ኢንዱስትሪ ውስጥ የተለያዩ ችግሮች እንደሚታዩ ሲገለጽ ሰነባብቷል፡፡ በወተት አቅራቢዎችና በወተት አቀነባባሪዎች መካከል ያለው የንግድ ግንኙነት ጤና ማጣቱ በወተት አቅርቦት ላይ ተፅዕኖ እየፈጠረ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት 34 ወተትና የወተት ተዋፅኦ ማቀነበበሪያዎች እንደሚገኙ ቢታወቅም፣ የወተት ግብይታቸው ግን ሕግና ሥርዓትን ባለመከተሉ ምክንያት ችግር እየፈጠረ መምጣቱ ይነገራል፡፡ ይህንን የሚቀርፍ ሕግ እየረቀቀ ቢሆንም በጥሬ ወተት ግብይት ላይ የሚታየው ችግር ግን ሕጉ እስኪፀድቅ ድረስ የሚያስታግስ መመርያ ሊወጣ ከአፋፍ ደርሷል፡፡ በዓሳና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር እየተዘጋጀ የሚገኘው ሕግ እስኪፀድቅ ድረስ፣ አዲስ አስገዳጅ መመርያ ለማውጣት ረቂቅ ተዘጋጅቶ የዘርፉ ተዋናዮች እንዲመክሩበት ተደርጓል፡፡

ሰሞኑን ለውይይት ቀርቦ ከነበረው ሰነድ መረዳት እንደሚቻለው፣ የወተት ኢንዱስትሪው በሚጠበቀው ደረጃ ዕድገት አለማሳየቱ ብቻ ሳይሆን፣ ግብይቱም ቢሆን ጤናማ እንዳልሆነ ነው፡፡ ወተት አቅራቢዎችና አቀናባሪዎች ይተዳደሩበታል የተባለው  ‹‹የጥሬ ወተት ግብይት ረቂቅ የመግባቢያ ሰነድ›› የተዘጋጀው በኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ዋናው ሕግ እስኪወጣ ድረስ ይህ ሰነድ እንደ ገዥ ሕግ እንዲያገለግል ለማድረግ ኢንስቲትዩቱ የሚመለከታቸውን አካላት ጠርቶ አወያይቷል፡፡

ለወተት ኢንዱስትሪው ዕድገት ማነቆ ከሆኑ ምክንያቶች መካከል የጥሬ ወተት ጥራት አንዱ ነው ተብሏል፡፡ የወተት አቅርቦት ጥራት ላለመሻሻሉ ዋነኛ ችግር ሆኖ የተገኘው ደግሞ በአገሪቱ የወተትና የወተት ተዋፅኦዎችን ጥራት ለማስጠበቅ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ አለመኖሩ ነው፡፡

የሕጉ አለመኖር ቁጥራቸው እያደገ የመጣውን የወተት ማቀነባበሪያዎች በዘፈቀደ እንዲሠሩ፣ የጥሬ ወተት አቅራቢዎችም ለምርት ጥራት ግድ እንዲያጡ፣ በጠቅላላው የወተት ምርት ግብይት እንዲዘባረቅ ማድረጉ ባለፈው ሳምንት በተካሄደው ውይይት ወቅት ተገልጿል፡፡

በወተት ኢንዱስትሪ ዙሪያ የሚታየው ችግር በዚህ ብቻ አያበቃም፡፡ ከጥሬ ወተት ግብይት ጀምሮ የወተት ማቀነባበሪያዎች ያመረቱትን ወተት እስከሚሸጡበት ደረጃ ባለው ሒደት በርካታ ክፍተቶች እንደሚታዩ ተጠቅሷል፡፡ የዋጋ ጉዳይም ትልቅ ችግር ይታይበታል ተብሏል፡፡ በአቅራቢዎችና በማቀነባበሪያዎች መካከል የሚፈጠረው አለመግባባትም ኢንዱስትሪውን ወደ ባሰ ችግር እየገፋው ይገኛል ተብሏል፡፡

በሁለቱ ተዋናዮች መካከል የሰፈነው አለመግባባትም ጥራት የጎደለው ምርት እንዲበራከት፣ ጥራት ላይ የተመሠረተ ግብይት እንዳይሰፍን ማድረጉ ይጠቀሳል፡፡ ይህም በአቅራቢዎችና በፋብሪካዎች መካከል ያለመግባባቱ እንዲሰፋ ማደረጉን በረቂቅ ሰነዱ የቀረበው መረጃ ይጠቅሳል፡፡

በዚህ አለመግባባት መነሻነትም ግብይቱን በሥርዓት ለመምራት ገዥ ሕግ እንደሚያስፈልግ ታምኖበት፣ አቅራቢዎችና ፋብሪካዎች የጥሬ ወተት ግብይት ሲፈጽሙ ሊከተሉት የሚገባውን አካሔድ የሚደነግግ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥም ወደ ተግባር እንዲገባ ተጠይቋል፡፡

ጥራትን መሠረት ያደረገ የወተት ግብይት ሥርዓት እስኪዘረጋ ድረስ ግን በአዲስ አበባና በዙሪያው በሚገኙ የወተት ፋብሪካዎችና አቅራቢዎች መካከል ለተፈጠረው አለመግባባት እልባት ለመስጠት ታስቦ በጊዜያዊነት የሚተገበር የጥሬ ወተት ግብይት የመገበያያ ሰነድ ወደ ሥራ እንዲገባ ማድረግ ግድ ብሏል፡፡

በኢንስቲትዩቱ የቀረበው መረጃ እንደሚያሳየው፣ በመስክ ከተሰበሰቡ መረጃዎች በመነሳት፣ የወተት ፋብሪካዎች የሚቀበሉት የጥሬ ወተት የቅባት ይዘት ከ2.3 በመቶ እስከ 3.4 በመቶ ባለው መጠን ሲሆን፣ ይህ የቅባት መጠን ግን ደረጃውን ያልጠበቀ ነው ተብሏል፡፡

ወተት አቅራቢዎች የወተትን መጠን ከፍ ለማድረግና አግባብነት የለውም የተባለ  ዋጋ ለማግኘት ሲሉ በጥሬ ወተት ውስጥ ውኃ መጨመርን ሥራዬ ብለው እንደተያያዙት ተጠቅሷል፡፡ የወተት መቀነባበሪያ ፋብሪካዎች በበኩላቸው ብዛት ያለው ጥሬ ወተት ለማግኘት ሲሉ ውኃ የተቀላቀለበትን ወተት እያወቁ ተገቢ ባልሆነ ዋጋ እንደሚረከቡ በመስክ ቅኝት በመረጋገጡ፣ አስቸኳይ ሕግ እንዲቀረጽ አስገድዷል ተብሏል፡፡ የጥሬ ወተት ግብይትን ችግሮች ያሳየው ጥናት፣ ውኃ የተቀላቀለበትን ወተት ከገበያ ዋጋ በተጋነነ አኳኋን አንዱን ሊትር እስከ 14.50 ብር እየገዙ እንደሚያቀነባብሩ አረጋግጧል፡፡

በአንፃሩ በአጽዋማት ወቅት የወተት ፋብሪካዎች አንድ ሊትር ወተት በዘጠኝ ብር ሒሳብ ከገበሬው እየገዙ ገበሬውን ማማረራቸውም ግብይቱን እንዳዛባው አይሳቷል፡፡ በረቂቅ ሕጉ መሠረት ሁለቱም ወገኖች እንዲስማሙና የጥሬ ወተት ግብይት ዋጋ ተመንም በወተት ውስጥ ባለው የቅባት መጠን ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ለማድረግ ባለፈው ሳምንት ከተደረገው ውይይት ባሻገር፣ በቀጣዩ ሳምንትም ሰነዱ በስምምነት ተፈርሞ ወደ ሥራ እንዲገባ ይደረጋል ተብሏል፡፡

በስምምነት ሰነዱ እንደ አስገዳጅ ከተቀመጡት ድንጋጌዎች ውስጥ የአንድ ሊትር ጥሬ ወተት ዋጋ በቅባት መጠን ላይ እንዲመሠረት የሚጠይቀው ነው፡፡ የ3.5 በመቶ የቅባት መጠን ያለው ወተት ከገበሬው ማኅበራቱ በጥናት ላይ ተመሥርቶ በሚወሰን ዋጋ መሠረት፣ የቅባት መጠኑ በመጨመረ ቁጥር ለ0.1 በመቶ የቅባት መጠን የ0.25 ብር ተጨማሪ ሒሳብ በዋጋው ላይ ተተምኖ ክፍያ እንዲፈጸም የሚለው ይገኝበታል፡፡

በሕግ የተደራጁ ማኅበራት ወይም ዩኒዬኖች ጥሬ ወተትን ከአባሎቻቸው ሰብስበው ለፋብሪካዎች ማቅረብ አንደሚችሉ የሚያመለክተው ይህ ረቂቅ ሰነድ፣ በወተት ውስጥ በተፈጥሮ ካለው 87 በመቶ የውኃ መጠን ተጨማሪ ውኃ መደባለቅ እንደማይገባ አስቀምጧል፡፡

ውኃ መቀላቀል፣ ከሌሎች ባዕዳን ነገሮችና የወተትን ጥራት በሚያጓድሉ ምክንያቶች አንዱ ፋብሪካ ጥራቱን መዝኖ የጣለውን ወተት ሌላው ፋብሪካ ወይም አቅራቢ ፈጽሞ መቀበል እንደማይችል በአስቸኳይ ሰነዱ ውስጥ ተካትቷል፡፡

አንድ የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ የጥሬ ወተት ፍላጎቱን ሊያሟሉለት የሚችሉ ወተት አቅራቢዎች ዘንድ መንደር ድረስ ወርዶ መግዛት እንደማይችል የሚጠቅስ ሲሆን፣ አምራቹ ግን ያመረተውን ወተት በቀጥታ ለፋብሪካ መሸጥ እንደሚችል አስፍሯል፡፡

ማንኛውም የወተት ማቀነባበሪያም ሆነ የወተት አቅራቢ የጥሬ ወተት የግዥ ሰነድንና ሌሎች መረጃዎችን በኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ባለሙያዎች በሚጠየቅበት ወቅት የማሳየት ኃላፊነትና ግዴታ ተጥሎበታል፡፡

አንደኛው ፋብሪካ የሌለውን ፋብሪካ ምርትና አገልግሎት ማጥላላትና ማንቋሸሽ በሕግ እንደሚያስጠይቅ የሚጠቅሰው ሰነድ፣ ማንኛውም የወተት ፋብሪካም ሆነ ሰብሳቢ የአንድን ድርጅት ተመሳሳይ ስም መጠቀም እንደማይችል አስፍሯል፡፡

ከወተት ጋር ተያዥነት ያለው ሥራ የሚሠራ ሰው በጥሬ ወተት ግብይት ጣቢያዎችና በወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ውስጥ ለወተት ጥራትና ደኅንነት የሚበጁ የደንብ አልባሳትን መልበስ ይጠበቅበታል፡፡

የወተት ፋብሪካዎች ወተት ሲረከቡ፣ የተረከቡትን የወተት መጠንና የወተቱን ይዘት በግልጽ ለወተት አቅራቢው ማሳየትና መረጃውን መስጠት እንዳለባቸው ተዘርዝሯል፡፡ ወተት አምራቾችም ሆነ የጥሬ ወተት አቅራቢዎች ወተት ማቅረብ የሚችሉት ለወተት ፋብሪካዎችና ሕጋዊ ፈቃድ ላላቸው ድርጅቶች ብቻ እንደሚሆን አስገዳጅ አሠራር ተቀምጦባቸዋል፡፡ እንዲህ ያሉ ይዘቶችን ያስተዋወቀው ሰነድ በአጭር ጊዜ እንዲፀድቅ ማሳሰቢያ ተሰጥቶበታል፡፡ በአሁኑ ወቅት 34 የወተት ማቀነባበሪያዎች  በቀን የሚያመርቱት 250 ሺሕ ሊትር  እንደሆነ ታውቋል፡፡