አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

ለሙስና የተጋለጡ አሠራሮችና ክፍተቶች

በያሲን ባህሩ

የመልካም አስተዳደርና የሕግ የበላይነት ጉዳይ ዋነኛ የመንግሥት ጥንካሬ መለኪያ ነው፡፡ እነዚህ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ዋነኛ ምሰሶዎች (ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና የሕግ ልዕልና) ጋር በእጅጉ የተሳሰሩ ጉዳዮች ለአገሮች ልማት መቀጣጠልም ሆነ፣ ለፍትሐዊ የሕዝብ ተጠቃሚነትና ተሳትፎ አስፈላጊዎች ናቸው፡፡

‹‹የመልካም አስተዳደር ማስፈን ጉዳይ አገር በመምራት ላይ ያለው መንግሥት ኃላፊነት ነው›› የሚባልበት ግልጽ ምክንያት ግን አለ፡፡ ይኸውም መልካም አስተዳደር የሚሰፍነው መንግሥት ባወጣው ግልጽ ፖሊሲና ሕግ፣ እንዲሁም በቢሮክራሲው አማካይነት በመሆኑ ነው፡፡ በዕርግጥ ሕዝቡም የአገር ግንባታው ዋነኛ ተዋናይ እንደመሆኑ፣ ሙስና እንዲዳከም ብሎም ፍትሕ እንዲረጋጋጥ የራሱ ሚና የለውም ሊባል አይችልም፡፡

የዛሬው ምልከታዬ በአገራችን ለሙስናና ለብልሹ አሠራር የተጋለጡ መሥፈርቶች፣ መመርያዎችና የማስተናገጃ ሥልቶችን ይመለከታል፡፡ ከሁሉ በላይ ካለበቂ ጥናትና ሕዝብ ያላሳተፈ ውሳኔ በግብዓታዊነት የሚፈጸሙ ዕርምጃዎችን አደገኛ ውጤትም ለመቃኘት እንገደዳለን፡፡ ይህ ሐሳብ ሁሉንም ዜጋና የሚመለከታቸውን የመንግሥት አካላት የሚያሳትፍ ስለሚመስለኝ፣ አንባቢያን ከልብ አጢነውት ሐሳብ እንድንለዋወጥበት እሻለሁ፤››

ግብር ‹‹በዘመቻ›› እየተሰበሰበ መራኮት

     በየትኛውም ዓለም የሚኖር ሰው ሠርቶ ካገኘው ገቢ አንደ አቅሙ ግብር የመክፈል ግዴታ አለበት፡፡ በእኛም አገር ቢሆን መርሁ ያውና አንድ ነው፡፡ ይሁንና በሠለጠነው ዓለም (እንደ ስካንዲቬኒያን አገሮች ባሉት) ግብር ለምንና ምን ያህል እንደሚከፈል የተረዳ ማኅበረሰብ አላቸው፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን የከፈሉት ግብር ለምን ሥራና እንዴት እንደዋለ በግልጽነትና በተጠያቂነት መርህ የሚያረጋግጡበት ሥርዓት ዘርግተዋል፡፡ በተቃራኒው የእኛን አገር ጨምሮ አብዛኛው ታዳጊ ማኅበረሰብ በግብር መክፈል ግዴታው ላይ ታማኝነት የለውም፡፡ መንግሥታቱም በተፅዕኖ የማስገደድና በዘመቻ ግብርን የመሰብሰብ ችግር ጎልቶ ይታይባቸዋል፡፡ ለነገሩ የተሰበሰበ የሕዝብ ሀብትም እየተዘረፈ የሚያበሰጭ ይሆናል፡፡

ከሰሞኑ የአገራችንን የንግዱን ማኅበረሰብ ክፉኛ ያስደነገጠ ‹‹የቀን ገቢ ግምት›› ይፋ ተደረጓል፡፡ በተጨባጭ እንዲታየው ይህ የቀን ገቢ ግምት በቀዳሚነት ወቅታዊነት የጎደለው ነው፡፡ አምስት ዓመትም ይዘግይ ስድስት ዓመት ለ2009 ዓ.ም. በሐምሌ ግብር ለመሰብሰብ በዚሁ ዓመት ሰኔ ላይ በግብረ ኃይል (ከተለያዩ መሥሪያ ቤቶች የተቋቋመ ኮሚቴ) መገመቱ ‹‹ሊበሏት ያሳደጓት . . . ›› አስተርቷል፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን መንግሥት በሕዝብ ቅሬታ ሲናወጥ ከርሞ የፖለቲካ አመረሩ ገና በተሃድሶና በሥልጠና ላይ በተጠመደበት ወቅት ላይ መሆኑም ‹‹ሕዝቡን ለመጫን›› የታለመ ተግባር አስመስሎታል፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ለተከታታይ ዓመታት በመጣበት ዕድገት ሳይቀጥል፣ በድርቅ ወቅትና የውጭ ምንዛሪ እጥረት ነጋዴውን ሲያናወዝ ይፋ መደረጉም የግብታዊ ዕርምጃ መገለጫዎች ነበሩ፡፡

ከዚህ ሁሉ በላይ ‹‹ነጋዴውን ያስደነገጠና ግራ ያጋባ›› የተባለለት ይህ ግመታ በየበረንዳው ቡና የሚያፈሉና የጉሊት ቲማቲም ቸርቻሪዎችን ሳይቀር በሺዎች የሚቆጠር ብር የቀን ገቢ ያላቸው አድርጎ መጥቷል፡፡ ባለመለስተኛ ሱቅ፣ የግሮሰሪ አገልግሎት ሰጪና ነጋዴ ሁሉም በተለጠጠ ስሌት ወደ ‹‹ለ›› ግብር ከፋይ ለመንደርደር ገፍቶዋቸዋል፡፡ የንግዱ ማኅበረሰብ ይቅርና ምሁራን፣ ፖለቲከኞች፣ የሲቪክ ማኅበራት መሪዎች . . . ሳይቀሩ ክፉኛ ተቃውመውታል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች (በምዕራብ ሸዋና በወለጋ ዞኖች፣ በአዲስ አበባ መርካቶና ኮልፌ) የንግዱ ማኅበረሰብ ተቃውሞውን በአድማ ጭምር አሳይቷል፡፡ በተናጠል ከገቢዎች ሠራተኞች ጋር ወደ ፀብ የገቡ፣ የንግድ ቤታቸውን በአንድ ምሽት ዘጋግተው የተሰወሩም ያጋጠሙ ሲሆን፣ ‹‹የመጣው ይምጣ ልንከፍል አንችልም›› ብሎ በተስፋ መቁረጥ የቆዘመውም ትንሽ አይደለም፡፡

‹‹ደሃ ይበላው እንጂ ይገብረው አያጣም›› በሚል ኋላቀር ፍልስፍና በድንገት ብድግ ብሎ የግብር ናዳ ማውረድ ለምን ተፈለገ? የሚለው ጥያቄ አነጋጋሪ የሆነውም ለዚሁ ነው፡፡ በአንዳንድ ታዛቢዎች መንግሥት ልማቱን እንዲያፋጥንና ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዲያደርግ ከፍተኛ የሕዝብ ጫና አለበት፡፡ ስለዚህ ሕዝቡም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲደረግ ግብርን አሟልቶ መክፈሉ የግድ ነው፡፡ ስለዚህ በንግዱ ማኅበረሰብ ላይ የተጣለው የቀን ገቢ ግምት መታየት ያለበት ታይቶ መተግበሩ አስፈላጊ ነው በማለት የሚነሳ ክርክር አለ፡፡

ሌሎች ደግሞ መንግሥት የቀን ገቢ እንዲገምቱም ሆነ ግብር እንዲያጣሩ የመደባቸው የራሱ ሠራተኞች ከሕዝቡ ጋር አጋጭተውታል፡፡ በቀን ከዕለት ጉርስ ያለፈ ገቢ የሌላቸውና በዕርዳታ የሚተዳደሩትን ሁሉ መሬት ላይ በሌላ አኃዝ በማስደንገጥ ተስፋ ከማስቆረጥ በዘለለ የሚገኝ ትርፍ የለም ባይ ናቸው፡፡ ዜጎች ከስደት ተመልሰው ይቋቋሙ፣ በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ ተደራጅተው ሥራ ፈጠራ ይበረታታ ሲል የከረመ መንግሥት ‹‹የግብር መረብ ለማስፋት›› ብሎ ዱብ ዕዳ ማውረዱ ጅምሩን የሚንድ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ እዚህ ላይ በከፍተኛ ፍጥነት የንግድ ፈቃድ ለመመለስ የተዘጋጀውን ኃይል በተመለከተ መከራከሪያው ውኃ እንደማያነሳ መረዳት ተገቢ ይሆናል፡፡ አስከፊው እውነታ ደግሞ በዘመቻ ሥራው የቀን ገቢ ግምትም ሆነ ግብር ለሚተምኑ ሰዎች ለመደራደርና ለሙስና በር እንዲከፈትላቸው ማድረጉ ነው፡፡ በአዲስ አበባ በቅርቡ እንደታየው የንግዱን ማኅበረሰብ ቅሬታ ለማዳመጥ እንኳን የሚለመኑና መደለያ የሚፈልጉ ሙያተኞች እንደነበሩ ነው፡፡ በአንዳንድ ክልሎችም ‹‹እኔ እንዲህ አደረግኩልህ›› ባዮች መታየታቸውንም ሕዝቡ እየተናገረ ነው፡፡ አሠራሩ ከክልል ክልል ወጥ አለመሆኑና ‹‹ሆን ተብሎ የተደረገ›› መምሰሉም የመልካም አስተዳደር ብሶቱንና ሙስናን የሚፈጥር እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ስለዚህ የቀን ገቢ ግምትም ሆነ የግብር አሠራሩ በጥናት ላይ ይመሥረት፡፡ ካድሬን ሳይሆን ሕዝቡን ያሳትፍ፣ ብዙኃኑን ያሳምን፡፡ ያለዚያ ግን ችግር ፈጣሪ መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ ለልማትም ሆነ ለዕድገት እንቅፋት ነው፡፡ ግብር መክፈል መብትም ግዴታም ነው፡፡ ነገር ግን የሞላጮች መጫወቻ እንዲሆን መፍቀድ አገርን ትርምስ ውስጥ መክተት ማስጠየቅ አለበት፡፡

‹‹ስታንዳርድ›› ተብዬዎችና መሥፈርቶች እየተንዛዙ ነው 

በአሁኑ ወቅት አነስተኛ ሬስቶራንት ወይም ሆቴል ለመከፈት ያሰበ ሰው የንግድ ፈቃድ ለማውጣት ከሦስት ወራት የማያንስ ጊዜ ይወስድበታል፡፡ አነስተኛ የማስታወቂያ ድርጅት ወይም ተዛማጅ ሥራ ልሥራ ቢልም ምልልሱ ቀላል አይደለም፡፡ አስከፊው የጊዜው መጓተት ብቻ ሳይሆን ከጤና ቢሮ፣ ከባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ ከንግድ ቢሮ . . . የሚወጣው መሥፈርት ፍፁም ተጨባጭነት የጎደለው፣ መሬት ላይ ያለውን እውነት ያላገናዘበና ሥራ ቦታው ድረስ ለማረጋገጥ ለሚመጣው ‹‹ባለሙያ›› (ነጭ ለባሽ ማለት ሳይሻለ አይቀርም) ጉቦ ከፍሎ መገላገልን የሚያበረታታ መሆኑ ነው፡፡

ለአብነት ያህል የተሟላ የመሥሪያ ቦታ በሌለበትና በውድ የቤት ኪራይ በየጥጋጥጉ የሚከፈቱ አነስተኛ ሆቴሎችን ‹‹ብቃት ለመመዘን›› ከምግብ፣ ከመድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ቢሮ የሚላከውን ‹ቼክ ሊስት› መጥቀስ ተገቢ ነው፡፡ አካባቢያዊ ሁኔታ ብሎ ከመኖሪያ ቤቶች፣ ከትምህርት ቤቶች፣ ከጤና ድርጀቶች. . . ያለው ርቀት፣ ከኢንዱስትሪ ብካይና ከቆሻሻ ያለው ርቀት ይልና ከመሠረተ ልማቶችም እንዲርቅ ያስገድዳል፡፡ ታዲያ ሆቴል የሚሠራው ሰማይ ላይ ካልሆነ በከተሞች ምን ላይ ሊቆም ይችል ይሆን? የድርጅት ስፋት፣ የአየር ዝውውርና የብርሃን ሁኔታ፣ የውኃ አቅርቦትና የመፀዳጃ ቤት ይዞታ አስፈላጊ ናቸው፡፡ የእጅና የገላ መታጠቢያ፣ ለጥበቃ ወይም ለማዕድ ቤት ሠራተኞች ሳይቀር የትምህርት ደረጃ፣ የሥልጠና አሰጣጥና ጤና አጠባበቅ እንዲሟላ መጠየቅ ክፍያውንና የሠራተኛውን ሁኔታ ያላገናዘበ ነው፡፡

የምግብ፣ የመጠጥ ማስቀመጫና መሸጫ ከ20 በላይ ዝርዝር መሥፈርቶችም ለፋብሪካና ለባለ ኮከብ ሆቴሎች እንጂ ማኅበረሰቡ ውስጥ ለሚገኝ ሬስቶራንት ሊሆኑ የማይችሉ ናቸው፡፡ አልባሳት፣ የአደጋ መከላከያና፣ የጤና አገልግሎት መስጫዎችም . . . የታየና የማይጨበጡ ናቸው፡፡ ታዲያ እነዚህን ሁሉ ‹‹ስታንዳርዶች›› አሟልቷል የሚል ወረቀት ለማግኘት መፍትሔው መደራደርና በእጅ መሄድ ቢሆን ምን ይደነቃል? ለዚህም ነው በየዓመቱ ቋሚ ክፍያ የሚቀበሉ ጉቦኛ ሙያተኞች ከልካይ ሳይኖርባቸው በየጽሕፈት ቤቱ ተቀምጠው የቀጠሉት፡፡

ከፋ ወዳለው የኢንቨስትመንት (በአገልግሎትም ሆነ በአምራች ዘርፍ) ሲገባም ውጥንቅጡ ያንኑ ያህል ነው፡፡ አዲስ አበባን ጨምሮ ብዙዎቹ ክልሎች ‹‹ባለሀብቶች ኑ! በራችን ክፍት ነው አልሙ!›› የሚል ጥሪ ያሰማሉ፡፡ ብሮሸር ይታተማል፣ ማስታወቂያ ይነገራል፣ በየባዛሩ ይለፈፋል፡፡ ገንዘብ ይዞ ለሥራ ጎራ ያለ ባለሀብት ግን የሚገጥመው መሰናክል ተነግሮ ተነግሮ ያልታረመ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ተስፋ አስቆራጭም ነው፡፡

አንዳንዶቹ በቅድመ ሁኔታና በተንዛዛ መሥፈርት ያሸማቅቃሉ፡፡ ሌሎቹም በጉዳይ ገዳይና በደላላ ካልሆነ ቀጥታ በር እንደሌለ በዘረጉት አጥር ያስገነዝባሉ፡፡ በነገራችን ላይ በገዳይ ገዳይነት ብቻ የበለፀጉ የውስጥ ደላሎችን ሁሉም ያውቃቸዋል፡፡ በግላጭ ጉቦ የሚጠይቁና የመሥሪያ ቦታ ለማመቻቸት የሚደራደሩ የመንግሥት ሹማምንትም ቁጥራቸው ትንሽ አይደሉም፡፡ የይስሙላ ኮሚቴ፣ ካቢኔ. . . ወሰነ በሚል ማደናገር የፈለጉትን ሲጠቅሙ፣ ያልተሰማማቸውን ሲበድሉ የሚታዩት ግልጽነትና ተጠያቂነት አልባ አካሄድ የፈጠራቸው ጉዶች ናቸው፡፡

በዚህ ረገድ መንግሥት ለማስተካከል የሞከራቸው ሥራዎች (እንደ ኢንዱስትሪ ፓርክና ሥርዓቶች) ቢኖሩም፣ ለውጭ ባለሀብትና ፌዴራል ላይ ብቻ የተንጠለጠሉ ናቸው፡፡ ዝርክርክ መሥፈርቶች ብቻ ሳይሆን የብሔር ፖለቲካው ሰለባ መሆኑም ዋነኛው ደንቃራ እንደሆነ መሸሸግ የጥፋቱ መንገድ ተባባሪ መሆን ነው፡፡

ከዚህ አንፃር መንግሥት ሙስንና፣ የመልካም አስተዳደር ዕጦትንም ሆነ ኢፍትሐዊነትን አስወግዳለሁ ካለ ሕገወጦችን ከማደንና መጠየቅ ባሻገር፣ ከነባራዊው ሁኔታ በመነሳት ሕዝቡን በሚያሳትፍ መንገድ አቅጣጫን መያዝ ብልህነት ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡

ሕግ አስከባሪው ተቆጣጣሪ ይደረግበት

በአገሪቱ ያለው ‹‹የፀጥታ ኃይል›› ቁጥር ብቻ ሳይሆን የበዛው ዓይነቱም ነው፡፡ በሌላው ዓለም ከሚታወቁት የመከለከያ ሠራዊት አባላትና የፌዴራል ፖሊስ በተጨማሪ ሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የየራሳቸው ፖሊስ ሠራዊት አላቸው፡፡ ከዚያም አልፎ አድማ በታኝ (ፈጥኖ ደራሽ)፣ ልዩ ኃይል፣ የትራፊክ ፖሊስ . . . ወረድ ሲልም የደንብ አስከባሪ፣ ሚሊሻና ‹‹ፖሊስ አጋዥ›› እየተባለ ከገጠር እስከ ከተማ በማኅበረሰቡ የተሰገሰገው የታጠቀም ይሁን ያለታጠቀ ኃይል በሚሊዮን የሚቆጠር ነው፡፡ ይህ እንግዲህ እንደ የአገር ውስጥ ደኅንነት፣ ፊናንስ ፖሊስ፣ አስተዳደር አካሉና የፍርድ ቤትን ሲቪል ሠራተኛ ሳይጨምር መሆኑ ነው፡፡

እዚህ ላይ መነሳት ያለበት ጉዳይ ታዲያ ይህ ሰፊ ኃይል ምን ያህል የተቀናጀ ነው? ሥነ ምግባሩና የሕዝብ አገልጋይነቱስ በምን ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው? የሚለው ነጥብ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ እንዳለው (የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይም ቆይተን ስለነበር) ከሕገ መንግሥቱ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ጥብቅ ድንጋጌዎች ወጣ ያሉ የመብት ጥሰቶች አጋጥመዋል፡፡ ዜጎች ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተይዘዋል፡፡ መንገላታትና ዱላ ያጋጠማቸውም ነበሩ፡፡ በአዲስ አበባ ደግሞ በፖሊስ ድብደባ የንፁኃን ሕይወት (ቢያንስ ሁለት ሰው) እንዳለፈም ተሰምቷል፡፡ ይህ ክፉኛ መወገዝ ያለበትና ወደኋላ እንዳይመለስና መቆም የሚገባው ውሽልሽል ተግባር ነው፡፡

በከተሞች (በተለይ በመዲናዋ) ያለው የደንብ አስከባሪ ኃይል ደሃ አባራሪና ነጣቂ የመሆኑ ችግርም መፈተሽ አለበት፡፡ ከድንበር አልፎ ሲመጣ ያልተያዘ ልባሽ ጨርቅ፣ በየሜዳው የሚቸረቸር ፍራፍሬና አትክልትን ከደሃ መዳፍ በመንጠቅ ግልጽነት በሌለው አሠራር ለግል ጥቅም ሲውል ይታያል፡፡ በየቀበሌውና ደንቦች ጽሕፈት ቤቶች በረንዳ ላይ እየተበተነ ለብልሽት የሚዳረገው የደሃ ገንዘብም ምሬትን የሚቀሰቅስ ካልሆነ በስተቀር ለአገር የሚበጀው ነገር የለም፡፡ በሕዝቡ ውስጥ በስፋት የሚነገረው ‹‹ወይ አንሳ፣ ወይ ሃምሳ›› የሚለው የሕገወጥ ‹‹ደንብ አስከባሪ›› መዝሙር ካልተቀየረ ሙስና እንደምን ሊቀረፍ ይችላል? ሕግ በማስከበር ስም ዜጎችን ማንገላታትና ንብረታቸውን መቀራመት በጊዜ ካልቆመ መዘዙ የከፋ ይሆናል፡፡

ሕገወጥ ግንባታን ለማስቆም የተደራጀው ግብረ ኃይልም ቢሆን የግለሰቦች ቤት ጣሪያ ለምን ተቀየረ? ወይም ግድግዳው ቀለም እንዴት ታደሰ? እያለ የሚደራደርበት ሥርዓት ፋይዳው እምኑ ላይ ነው፡፡  

በተለይ በፊንፊኔ ልዩ ዞን የአዲስ አበባ ዙሪያ ከተሞች የተደራጀው ‹‹ፖሊስ አጋዥ›› ተባለ ኃይልም ፍትሕን የሚያዛባና ተቆጪ የሌለው ሆኗል፡፡ በሰበታ ከተማና ዙሪያው እንደታየው የአዲስ አበባ፣ የኦሮሚያ ድንበር እያለ ዜጋ የሚያንገላታ፣ በብሔር አጥር ተጆብኖ የሕዝብ ምሬትን የሚቆሰቁስ፣ የግልና የቡድን ጥቅም የሚያሳድድ እየሆነ ስለመምጣቱ ይደመጣል፡፡ ግን የትኛው የማሻሻያ ዕርምጃ ተወሰደ?!

በመንገድ ትራንስፖርት ዘርፍ ላይ እየተባባሰ ለመጣው የትራፊክ አደጋም ሆነ ለመልካም አስተዳደር ዕጦት የትራፊክ ፖሊሶች ሚና የጎላ መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ በተለይ በክልሎች (በኦሮሚያና በደቡብ፣ በሶማሌና በአፋር ይብሳል) ያለው የመንገድ ትራንስፖርት ማኔጅመንት ለከፋ ሙስና የተጋለጠ ነው፡፡ በተለያዩ አሽከርካሪዎችና ባለንብረቶቸ ተደጋግሞ እንደሚገለጸው በእነዚህ ክልሎች በመገጨትም ሆነ በመገልበጥ የትራፊክ አደጋ የደረሰበት አሽከርካሪ የኢንሹራንስ መረጃ ለማግኘት ከአሥር ሺሕ እስከ 50 ሺሕ ብር ጉቦ መክፈል ግዴታው ነው፡፡ ይህን ገንዘብ ለአንድ ትራፊክ ፖሊስ የሚሰጥ ብቻ ሳይሆን፣ በአንዳንዱ አካባቢ ከመርማሪ እስከ ፖሊስ አዛዥ ድረስ የሚከፋፈል መሆኑ ሲታወቅ ወዴት እየሄድን ነው? ያስብላል፡፡ እጅግ የሚያሳዝን ነው፡፡

ሥነ ምግባር የጎደላቸው የትራፊክ ፖሊሶች በተለያዩ ሰበቦች ‹‹የዕለት ገቢ ለመሰብሰብ›› ብለው በተለይ ከንግድና ከጭነት አሽከርካሪዎች የሚቀበሉት ጉቦ ‹‹ተብሎ ተብሎ›› መፍትሔ ያጣ ነው፡፡ እዚህም ላይ አሽከርካሪዎች በሕጋዊ መንገድ ላጠፉት ጥፋት የሚቀጡት ዋጋ ጉቦ ከሚከፍሉት በእጥፍ የሚበልጥ በመሆኑ፣ የቅጣት ሥርዓቱም ውጣ ውረድ የበዛበትና ጊዜ በል በመሆኑ እንደሆነ ይሰማል፡፡

ከዚህ አንፃር አብዛኛው ሕዝብ ‹‹ጉቦ የማይቀበለው የትራፊክ ፖሊስ ፓስተር ላይ የተለጠፈው ባለ ነጭ ቆብ ሥዕል ብቻ ነው›› እስከ ማለት ደርሷል፡፡ ይሁንና በጅምላ መፈረጁ እምብዛም የማይጠቅመው ለሙያ ሥነ ምግባራቸው የታመኑ አብዛኛዎቹ ሴት ፖሊሶችና ጥቂት ወንድ ፖሊሶች እንዳሉ ባይካድ መልካም ነው፡፡ የሥራ መስኩ ዋነኛ የሙስና በርና የሕዝብ መማሪያ ነው የሚለው ግን ለድርድር የማይቀርብ ሀቅ ነው፡፡

በአጠቃላይ በአገራችን የፀረ መስና ትግሉ አመርቂ አይደለም፡፡ ለወጉ ብልጭ ድርግም እያለም ቢሆን ይፍገመገማል፡፡ ይሁንና ሙስና ማለት ከፍተኛ የአገር ሀብት መዝረፍ ብቻ እንዳልሆነ ግንዛቤ መያዝ አለበት፡፡ በሁሉም አገር እንደሚታወቀው አነስተኛ ሙስና የሕዝቡን ምሬት ለማባባስና ሥርዓቱን ተዓማኒነት ለማሳጣት የሚያጋልጥ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በየአካባቢው በጉቦና በሙስና የብዙኃኑና ደሃ እንግልትና ጣር እየጨመረ ሆዱን የሚሞላው ሁሉ መጋለጥ አለበት፡፡ በሕዝብም ብርቱ ትግል ጭምር ማለት ነው፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን መንግሥት ለሙስና የሚያጋልጡ አሠራሮችን መድፈንና ግልጽነት/ተጠያቂነት ማስፈኑ ላይ ማተኮር ይገባዋል፡፡ ሁልጊዜም ቢሆን ለጊዜያዊ ፖለቲካ ሳይሆን ለአገርና ለሕዝብ ጥቅም ሊታገልም ግድ ይለዋል፡፡  የሙስና ተዋናዮች እንደ ልብ እየፈነጩ ትንንሽ ዓሳዎች ላይ ማተኮርም የፖለቲካ ሙስና ይሆናል፡፡ ሙስና ግንዱን ሲመቱት ቅርንጫፉም ጭምር ይገነጣጠላል፡፡ ከላይ ከላይ በማስመሰል ከሆነ ደግሞ ሥርዓቱን ጭምር እንደ ነቀዝ ይበላዋል፡፡

 

 ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡