አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

ምርት ገበያው ተጠባባቂ ሥራ አስፈጻሚ ተሾመለት

 

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ተጠባባቂ ሥራ አስፈጻሚና በአዲስ መዋቅር ሁለት ምክትል ሥራ አስፈጻሚዎች ተሰየሙለት፡፡ በቅርቡ የሥራ መልቀቂያ ማስገባታቸው የተገለጸውን የምርት ገበያውን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጨምሮ፣ ሌሎች ሁለት የምርት ገበያው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የስንብት ደብዳቤ ደረሳቸው፡፡

ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ወገኖች የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ ምርት ገበያውን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ሲመሩ ከቆዩት አቶ ኤርሚያስ እሸቱ በተጨማሪ በምርት ገበያው ቦርድ ውሳኔ እንዲሰናበቱ ደብዳቤ የተጻፈላቸው የምርት ገበያ የመጋዘንና ጥራት ቁጥጥር ኃላፊ ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ምክሩ ደንቢና የሰው ኃይል ዲፓርትመንት ኃላፊው አቶ ማኅተመ ከበደ ናቸው፡፡

የምርት ገበያው ቦርድ ለከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎቹ የስንብት ደብዳቤ ከጻፈ በኋላ፣ አቶ በላይ ጎርፉ የምርት ገበያው አዲሱ ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው እንዲሠሩ  መመደቡ ታውቋል፡፡ በተመሳሳይ ቦርዱ አቶ መርጊያ ባይሳን የምርት ገበያው የመጋዘንና ምርት ጥራት ቁጥጥር ኃላፊና ተጠባባቂ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ሆነው እንዲሠሩ መድቧል፡፡ አቶ መርጊያ ምርት ገበያው ከመጋዘን አገልግሎት ጋር ከመወሀዱ በፊት የመጋዘን አገልግሎት ድርጅትን በምክትል ሥራ አስፈጻሚነት ሲያገለግሉ የቆዩ ናቸው ተብሏል፡፡ የግብይት ዘርፉን በጊዜያዊነት እንዲመሩ የተሰየሙት አዲሱ ምክትል ተጠባባቂ ሥራ አስፈጻሚ ደግሞ አቶ በኃይሉ ንጉሤ ናቸው፡፡ ይኼ ምደባ ምርት ገበያው አዲስ የሥራ መደብ የፈጠረበት ሆኗል፡፡ ምክንያቱም እስካሁን ባለው አሠራር ምርት ገበያው የምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ መደብ አልነበረውም፡፡ ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ በላይ ምርት ገበያውን ከመቀላቀላቸው (እ.ኤ.አ. 2013) ቀደም ብሎ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የፋይናንስ ዘርፍ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ እንዲሁም የስትራቴጂክ ማኔጅመንት ዳይሬክተርና የኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ በመሆን ሠርተዋል፡፡ ከዚህም በላይ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የፕሬዚዳንቱ አማካሪ ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡

ከንግድ ባንክ አገልግሎታቸው ባሻገር በቀድሞ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ውስጥ የግዥ ተቆጣጣሪ ሆነው ያገለገሉት አቶ በላይ፣ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በቢዝነስ ማኔጅመንት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡ እንዲሁም ከኔዘርላንድ ማስትሪች የቢዝነስ አስተዳዳር ትምህርት ቤት የድኅረ ምረቃ ዲፕሎማ በባንክና በፋይናንስ የቢዝነስ አስተዳደር፣ የማስተርስ ዲግሪያቸውን ደግሞ ከእንግሊዝ በርኒንግሃም ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡

የምርት ገበያውን ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ይዘው የቆዩት ተሰናባቾቹ ኃላፊዎች በቦርዱ በተጻፈ ደብዳቤ ከኃላፊነታቸው እንዲለቁ የተደረጉት፣ ከሳምንታት በፊት የተደረገውን ግምገማ ተከትሎ ባስገቡት የመልቀቂያ ደብዳቤ መሠረት ነው፡፡ በዚህ ሳምንት የስንብት ደብዳቤ ሲደርሳቸው ከኃላፊነታቸው የለቀቁበት ምክንያት ተብሎ የተጠቀሰው፣ በጠየቁት የሥራ መልቀቂያ መሠረት የሚል ነው፡፡

እንደ መረጃው ቦርዱ ተጨማሪ የኃላፊዎችና የሠራተኞች ምደባ የሚያደርግ ሲሆን፣ ይህንን ምደባ እስከ መስከረም 30 ቀን 2010 ዓ.ም. አጠናቆ ያሳውቃል ተብሏል፡፡

አሁን በውክልና የተሰየሙት ሦስቱ የምርት ገበያው ኃላፊዎች ምደባቸው መፅናት አለመፅናቱ የሚታወቀው፣ እስከ መስከረም 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከዘጠኝ ዓመታት በላይ ዕድሜ ያለው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ እስካሁን በሦስት ሥራ አስፈጻሚዎች ሲመራ የቆየ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህ ሳምንት በጊዜያዊነት የአቶ ኤርሚያስን ቦታ ተክተው እንዲሠሩ የተመረጡት አቶ በላይ ምደባቸው ከፀና፣ አራተኛው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ይሆናሉ፡፡