አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

ክቡር ሚንስተር

[የክቡር ሚኒስትሩ ሚስት ስልክ ደወሉላቸው]

 • ምነው ብሩን ጠዋት ሳትሰጠኝ ወጣህ?
 • የምን ብር?
 • የድግሱን ነዋ፡፡
 • የምን ድግስ ነው የምታወሪው?
 • የእህቴ ልጅ ልትመረቅ መሆኑን ነግሬህ አይደል እንዴ?
 • እሱማ ነግረሽኝ ነበር፡፡
 • እስካሁን በጀቱን ከቢሮ አላስፈቀድኩም እንዳትለኝ?
 • ወይ በጀት?
 • ስማ አንድ ሺሕ ሰው ልጠራ ነው ያሰብኩት?
 • እየቀለድሽ ነው?
 • ምን ችግር አለው? አንተ ከቢሮ ሁለት ድንኳን ታስመጣለህ፣ ከዚያ ሦስት ሠንጋ መጣል ነው፡፡
 • ይኼ ሁላ ከየት ይመጣል?
 • ከመሥሪያ ቤት በጀት አስለቅቅ፡፡
 • ወይ ጣጣ፡፡
 • ስማ በአብዛኛው የሚጠራው እኮ ባለሀብትና ባለሥልጣን ስለሆነ ድግሱን ስም እናወጣለታለን፡፡
 • ምን ብለን?
 • ልማታዊ ድግስ፡፡
 • አዲስ መመርያ ወጥቷል ሴትዮ፡፡
 • የምን መመርያ?
 • እንደዚህ ዓይነት ድግሶች የሚከለክል፡፡
 • ስማ መስሚያዬ ጥጥ ነው፡፡
 • ምን እያልሽ ነው?
 • ማን ደግሶ ማን ይቀራል?
 • አልገባኝም?
 • እነሱ ልጆቻቸውን አስመርቀው ከጨረሱ በኋላ መመርያ ማውጣት ምን ይባላል?
 • ምንም ማድረግ አልችልም፡፡
 • ቀስ ብለው የውጭ ጉዟችንንም ይከለክሉናል?
 • አልሰሜን ግባ በለው አሉ፡፡
 • ማለት?
 • የውጭ ጉዞም ተከልክሏል፡፡
 • ይኼማ ሊደረግ አይችልም?
 • ተደረገ እኮ ነው የምልሽ?
 • ባለፈው ሳምንት እኮ ነው የአሜሪካ ቪዛችንን ያሳደስነው፡፡
 • ምን ላድርግ ታዲያ?
 • አሁንስ አልበዛም እንዴ?
 • ወይ ጣጣ፡፡
 • አሁን ልጆቹን ምን ልንላቸው ነው?
 • በቃ የአሜሪካ ጉዞ እንደቀረ ንገሪያቸው፡፡
 • ስማ መቼም አያናግሩኝም፡፡
 • ምን ይሻላል ታዲያ?
 • አሜሪካም ባይሆን ሌላ ቦታ እንውሰዳቸው፡፡
 • ሌላ የት?
 • ዱባይ፡፡
 • ውጭ አገር የሚባለውማ ከጥያቄ ውጪ ነው፡፡
 • ታዲያ ልጆቹ የት ሄደው ይዝናኑ?
 • አገር ቤት፡፡
 • አገር ቤት? ለምን አትጥሰውም ታዲያ?
 • ምኑን?
 • መመርያውን፡፡
 • የሚጠብቀኝን ታውቂዋለሽ፡፡
 • ታዲያ ከሕዝቡ በምን ልትለይ ነው?
 • አልገባኝም?
 • እንደዚህ ዓይነት ጥቅማ ጥቅም ካላገኘህ ምን ይሠራልሃል?
 • ምኑ?
 • ሚኒስትርነቱ!

[ለክቡር ሚኒስትሩ የአንድ ማተሚያ ቤት ባለቤት ደወለላቸው]

 • የጠፋ ሰው ከየት ተገኘህ?
 • ደርሷል ለማለት ነው የደወልኩት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምኑ ነው የደረሰው?
 • ካላንደሩና አጀንዳው፡፡
 • ምን?
 • ምነው ደነገጡ?
 • ከቢሮ አልደወሉልህም እንዴ?
 • እኔ እኮ እንዳይደውሉልኝ ብዬ ሌላ ሥራ አቁሜ ነው የእርስዎን ሥራ ያስቀደምኩት፡፡
 • ወይ ጣጣ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር በጣም እንደሚወዱት እርግጠኛ ነኝ፡፡
 • እ…
 • አጀንዳው በስምዎት ነው የታተመው፡፡
 • ወይ ጉድ፡፡
 • ክፍያው ሲፈጸም የእርስዎንም እፈጽማለሁ፡፡
 • ምን?
 • ኮሚሽን!

[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን ቢሮ አስጠሩት]

 • ፈለጉኝ ክቡር ሚኒስትር?
 • የአዲስ ዓመት አጀንዳዎቹ ታተሙ?
 • አዲሱ መመርያ አልደረሰዎትም እንዴ?
 • የምን መመርያ ነው?
 • በመመርያው መሠረት ከዚህ በኋላ አጀንዳ ማሳተም አንችልም፡፡
 • ባለፈው እሱን ሥራ እኔ ወስጄ አጀንዳዎቹ ታትመዋል፡፡
 • እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን ታፈጣለህ?
 • ያስጠይቀናል ብዬ ነው፡፡
 • ማን ነው የሚጠይቀን?
 • ኦዲተር ነዋ፡፡
 • ለምን ተብሎ?
 • ወጪ ቀንሱ ተብሎ ፎርም ተልኮልናል፡፡
 • እና ወጪ የምንቀንሰው አጀንዳ ባለማሳተም ነው?
 • እህሳ?
 • ስማ ወጪ የሚቀነሰው ሌላ ነገር በመቀነስ ነው፡፡
 • ሌላ ምን?
 • ሠራተኛ!

[ለክቡር ሚኒስትሩ በሰሞኑ የሙስና ዘመቻ ንብረታቸው ከታገደባቸው ባለሀብት አንዱ ይደውላል]

 • ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ማን ልበል?
 • ድምፄም ጠፋዎት?
 • ማን ነህ?
 • ያኔ በየቀኑ ምሳና እራት እንዳልበላን ድምፄም ጠፋዎት?
 • አንተ ውሽማዬ ነህ እንዴ ከእኔ ጋር ምሳና እራት ትበላ የነበረው?
 • ተውት እስቲ፡፡
 • ለማንኛውም ስልኩን ሳልዘጋው ማንነትህን ተናገር?
 • ልጅዎን ውጭ የማስተምረው ሰውዬ ነኝ፡፡
 • ውይ የእኔው ጉድ ነህ እንዴ?
 • እንደዚህ ዘንግተውኛል?
 • በስልክህ ለምን አልደወልክልኝም?
 • አልሰሙም እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
 • ምኑን?
 • ንብረቴ እኮ ታግዷል፡፡
 • ምን?
 • አዎ ከሰሞኑ የሙስና ዘመቻ ጋር በተያያዘ ንብረቴ ታግዷል፡፡
 • አንተ ሙስናው ውስጥ አለህበት እንዴ?
 • ኪኪኪ…
 • ምን ያስቅሃል?
 • ወደው አይስቁ አሉ፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • ለባለሥልጣናት የምሰጠው ስጦታ ራሱ ሙስና መሆኑን አያውቁም እንዴ?
 • በል ራስህን እዛው ቻል?
 • ምን እያሉ ነው?
 • ማንን ለማነካካት ነው?
 • እሱማ የማይነካካ ማንም አይኖርም፡፡
 • እና እኔንም ሙሰኛ ልትለኝ ነው?
 • እሱን ወደፊት የምናየው ጉዳይ ይሆናል፡፡
 • አልገባኝም እስቲ አብራራልኝ?
 • እኔን ከረዱኝ ሙሰኛ ላይሆኑ ይችላሉ፡፡
 • ምንድን ነው የምትቀባጥረው?
 • ክቡር ሚኒስትር ተደብቄ ነው ያለሁት፡፡
 • ለምን?
 • መንግሥት በንብረቴ ከመጣ ለእኔም እንደማይመለስ ገብቶኛል፡፡
 • ታዲያ እኔ ምን ላድርግህ?
 • እንዲረዱኝ ነዋ፡፡
 • ምንድን ነው የምረዳህ?
 • ሀቀኛ ባለሀብት መሆኔን አሳውቀው ከነገሩ ነፃ ያውጡኝ?
 • ሥራህ ነው ነፃ የሚያወጣህ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እኔም ቤተሰቤም ተረብሸናል፡፡
 • ታዲያ እኔን ሰላምና መረጋጋት ነው ያለህ ማን ነው?
 • ቀልዱን ትተው ቢረዱኝ መልካም ነው፡፡
 • እያስፈራራኸኝ ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር በችግርዎ ጊዜ እንደደረስኩልዎ ያውቃሉ፡፡
 • ታዲያ ሰው መርዳት ባህላችን ነው፡፡
 • አሁን እኔም ችግር ላይ ስለሆንኩ የእርስዎን ዕርዳታ እሻለሁ፡፡
 • አንተ የሚያስፈልግህ ዕርዳታ ሳይሆን ፀሎት ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ነገሮች ፈር ሳይለቁ ቢረዱኝ ጥሩ ነው፡፡
 • ባልረዳህስ?
 • ተያይዘን…
 • እ…
 • እንገባታለን!

[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ የውጭ ስልክ ተደወለላቸው]

 • ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ማን ልበል?
 • ወዳጅዎ ነኝ፡፡
 • ባለፈው ሳምንት ደውለህልኝ አልነበር እንዴ?
 • መሄዴን መናገር ስላልፈለግኩ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • የት ነው ያለኸው?
 • ዱባይ ነኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ሥራ አለህ እንዴ?
 • ትንሽ ልረፍ ብዬ ነው፡፡
 • ሰሞኑን አይደል እንዴ ከአሜሪካ ዕረፍት የመጣኸው?
 • ክቡር ሚኒስትር በአንዴ እኮ ነው የጨመረብኝ?
 • ግብር ነው?
 • ኧረ ስኳርና ደሜ፡፡
 • እና ዱባይ ልታስቀንስ ነው የሄድከው?
 • እንዴ በአንዴ ስታስገቧቸው ሁላችንም ደነበርን፡፡
 • ከማን ጋር ነው የሄድከው?
 • ከእርስዎ ጋር ቢዝነስ የሚሠሩ በሙሉ እዚህ ናቸው፡፡
 • ለምን ሄዳችሁ?
 • ፈርተን ነዋ፡፡
 • ምንድነው የሚያስፈራችሁ?
 • ክቡር ሚኒስትር ቢያስገቡንስ?
 • ማን አባቱ?
 • አይ አሁን እንደዚያ የሚባልበት ጊዜ አይደለም፡፡
 • ስማ እናንተ እኮ ልማታዊ ባለሀብቶች ናችሁ፡፡
 • ቢሆንም የጥንቸሏ ነገር እንዳይፈጸምብን ብለን ነው፡፡
 • ጥንቸሏ ምን ሆነች?
 • እስኪጣራ ተብለን እንዳንበሰብስ ነው፡፡
 • ምኑ ነው የሚጣራው?
 • ልማታዊነታችን፡፡
 • አሁን እዚያ ማን ማን አለ?
 • የእርስዎ ወዳጅዎች አንድም አልቀሩ፡፡
 • ምን እያደረጋችሁ ነው?
 • ይኸው ፌስቡክ ላይ አፍጥጠን ነው የምንውለው፤ እንዲያውም እኔ እዚህም ሥራ አልፈታሁም፡፡
 • ምን እየሠራህ ነው?
 • ውርርድ፡፡
 • የምን ውርርድ?
 • ቀጥሎ ደግሞ እናንተን ነው የሚከቱት እያልኩ ገንዘብ እያስያዝኩ ብዙ በላሁ፡፡
 • እውነትም ንግድ ደምህ ውስጥ ነው ያለው፡፡
 • ምን ላድርግ ክቡር ሚኒስትር?
 • ሰሞኑን ግን የሚታሰር ሰው ብዙም የለም፡፡
 • የእኔም ገቢ ቀዝቀዝ ብሏል፡፡
 • ለመሆኑ በቀጣይ ማን ነው የሚታሰረው?
 • እርስዎ!