አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

የጥፋት እጆች ይሰብሰቡ!

 

የንፁኃን ደም አይፍሰስ፡፡ በንፁኃን ደም እጃቸውን የሚታጠቡ በሕግ ይዳኙ፡፡ ንፁኃንን ከቀዬአቸው ማፈናቀል ይቁም፡፡ የንፁኃንን ሕይወት እያተራመሱ መረማመጃ የሚያደርጉ በሕግ ይባሉ፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በጨዋነት፣ በአርቆ አሳቢነትና በማስተዋል ከዘመን ወደ ዘመን እያሸጋገሩ ያኖሯትን አገር ስግብግቦችና ኃላፊነት የማይሰማቸው መጫወቻ አያድርጓት፡፡ ይህችን ታላቅ አገር በዓለም አቀፍ አደባባይ አንገቷን ለማስደፋትና ለማሸማቀቅ ለሚያሴሩባት የዘመናት ጠላቶቿ በቀላሉ ዒላማ እንድትሆን መፈቀድ የለበትም፡፡ ኩሩዎቹና ጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን በመከባበርና በመተሳሰብ የኖሩባት አገር የጥፋት እጆች ሰለባ እንድትሆን መፍቀድ በታሪክም በትውልድም ያስጠይቃል፡፡ ኢትዮጵያ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ልጆች እኩል እናት መሆኗ በተግባር እንዲረጋገጥ ከተፈለገ፣ ማዶ ለማዶ ሆነው የሚዛዛቱና የሚሻኮቱ ተገዳዳሪዎች ወደ አቅላቸው መመለስ አለባቸው፡፡ አገር በኩርፊያ፣ በጥላቻ፣ በቂምና በበቀል በተበከሉ ልቦች ትጠፋለች እንጂ አትኖርም፡፡ የዘመናት ጠባሳዎችን እያከኩና ከሥልጣን ጥም በላይ የሆነችን ታላቅ አገር ግዙፍ ምሥል እያንቋሸሹ መቀጠልም ለማንም አይበጅም፡፡ አጓጉል የምላስ ወለምታዎችና የጥፋት እጆች አደብ ይግዙ፡፡

ይህች ታላቅ አገር ለዘመናት ከተተበተበችበት ድህነትና ኋላቀርነት ብቻ ሳይሆን፣ እኔ ብቻ ነኝ የማውቅልህ ከሚባለው ጎታችና አጥፊ ጀብደኝነትም መላቀቅ አለባት፡፡ ከእንዲህeza

 ዓይነቱ ኋላቀርነት መላቀቅ የሚቻለው ደግሞ ከምንም ነገር በላይ ለሕግ የበላይነት በመገዛት ነው፡፡ ሕግ ሲከበር አገር በሥርዓት ይተዳደራል፡፡ መንግሥትም ሕግ ማውጣት ብቻ ሳይሆን የማክበርና የማስከበር ግዴታም አለበት፡፡ የሕጎች ሁሉ የበላይ ከሆነው ሕገ መንግሥት በተፃራሪ ሥልጣንን ለማመቻቸት ብቻ ሲባል አፋኝ ሕጎች መውጣት የለባቸውም፡፡ በሕገ መንግሥቱ ዋስትና የተሰጣቸው ሁሉም መሠረታዊ መብቶች መከበር አለባቸው፡፡ ዜጎችም በትክክል በሕግ ፊት እኩል መሆናቸውን በተግባር ሊያረጋግጡ ይገባል፡፡ ባለጊዜ እንደፈለገ እየፏለለ ሌላው ዜጋ ባይተዋርነት እንዲሰማው ከተደረገ የሕግ የበላይነት የለም፡፡ አንዱ በተጠየቀበት የሙስናም ሆነ ሌላ ወንጀል ሌላው ዝም ከተባለ ስለሕግ የበላይነት መነጋገር አይቻልም፡፡ ፍትሕ ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ ካልሆነ ሕገወጥነት ነግሷል ማለት ነው፡፡ በሥራ ምደባ፣ ሹመት፣ ጥቅማ ጥቅሞች፣ በትምህርት ዕድልና በመሳሰሉት ፍትሐዊነት ከጠፋ ችግር እንደሚከተል ተደጋግሞ ታይቷል፡፡ ወጣቶች ተስፋ አጥተው የመከራ ኑሮ ሲገፉ ሰላም አይኖርም፡፡ አድሏዊና አግላይ አመለካከቶች የተጫኑት ብልሹ አሠራር ሲበዛ ግጭት ይቀሰቀሳል፡፡ ይህንን ዓይነቱን ዝንፈት አለማስተካከል ዕዳው ለአገር ነው፡፡ የጥፋት እጆችን ያበረታታል፡፡

      መንግሥት ሕዝብን አላዳምጥም እያለ ከራሱ ብቻ ጋር እየተነጋገረ መቀጠሉ እንደማያዋጣ ከበቂ በላይ ትምህርት ተገኝቷል፡፡ ሕዝብን መናቅ፣ ምን ያመጣል ማለትና እንደፈለጉ መሆን የማይቻልበት ዘመን ላይ ነን፡፡ ይህንን በአግባቡ መረዳት ከተቻለ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ማክበርና ማስከበር፣ ብልሹና ሕገወጥ አሠራሮችን ከመሠረታቸው መንግሎ መጣል፣ በሕግ ዋስትና ያገኘውን የመደራጀት መብት አለመጋፋት፣ ዜጎች በነፃነት የመሰላቸውን እንዲናገሩ ወይም እንዲጽፉ ምኅዳሩን ነፃ ማድረግ፣ የሥልጣኑ ዋነኛ ባለቤት የሆነው ሕዝብ የፈለገውን እንዲመርጥ፣ የማይፈልገውን እንዲጥል ነፃና ዴሞክራሲያዊ ዓውድ መፍጠርና ለሕዝብ ብቻ መገዛት የአገር ባህል መሆን አለበት፡፡ መነጋገርና መደማመጥ የሰፈነበት አገር የሚገነባው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡ ይህ ሳይሆን ሲቀር ኩርፊያው ወደ አላስፈላጊ ጎዳና እያመራ ነውጥና ግጭት ይቀሰቅሳል፡፡ የንፁኃን ደም ይፈሳል፡፡ አቅመ ደካሞች፣ አረጋውያንና ሕፃናት ሳይቀሩ የቀውሱ ሰለባ ይሆናሉ፡፡ ይህ የጥፋት መንገድ በፍፁም እንዳይከሰት የጥፋት እጆች መሰብሰብ አለባቸው፡፡

በሌላ በኩል በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሥልጣን ላይ ካለው መንግሥት ጋር ጉዳይ አለን የሚሉ ወገኖች አገርን ከማተራመስና ሕዝብን ግራ ከማጋባት ሊታቀቡ ይገባል፡፡ በመጀመርያ የሥልጣኑ ባለቤት የሆነውን ሕዝብ ማክበር አለባቸው፡፡ እነሱ በርቀት ሆነው የሚቀሰቅሱት ግጭት ንፁኃንን ለአደጋ የሚያጋልጥና የአገርን ህልውና የሚያናጋ ከሆነ ለሕዝብ ፋይዳ የላቸውም፡፡ ከእነሱ በተቃራኒ ያለን ኃይል በጭፍን ለማስወገድ የሚያደርጉት ጥረት ሕዝብን ለዕልቂት አገርን ለውድመት የሚዳርግ ውጤት ካለው፣ አገርንና ሕዝብን እንዴት መታደግ ይቻላል? ሥልጡንና ዴሞክራሲያዊ አቀራረብ ሳይኖራቸው በጥላቻና በቂም በቀል ዓረም ውስጥ ሆነው መነጋገርና መደማመጥ እንዴት ይቻላል? ከአሉባልታና ከቀቢፀ ተስፋ ያልተላቀቀ አመለካከት እያራመዱና የዓመታት ስህተቶችን እየደጋገሙ ፖለቲካ ውስጥ መንደፋደፍ እስከ መቼ ይዘለቃል? የፖለቲካ ትግል እልህ አስጨራሽ፣ ትዕግሥት የተሞላበት፣ ሁለገብ ዕውቀትና ጥበብ ከማስተዋል ጋር ካላዋሀደ በግትርነት የጥላቻ መርዝ መርጨት ለአገር አይጠቅምም፡፡ ሌላው ቀርቶ የፖለቲካ ፓርቲነት ተክለ ሰውነት ሳይኖራቸው በግለሰቦች የሚመሩ ሱቅ በደረቴ ዓይነት ፋይዳ ቢስ ፓርቲዎች መብዛትስ ምን ይረባል? ከዓለም አቀፍ ተጨባጭ ሁኔታዎችና አገር ውስጥ ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር ያልተገናዘበ ጥሬ አስተሳሰብ ለአገርና ለሕዝብስ ፋይዳው ምንድነው? ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በስፋት የሚስተዋሉ በዘረኝነት የታጀቡ ቅስቀሳዎችስ ለማን ይበጃሉ? የጥፋት እጆች እነዚህንም ያካትታሉ፡፡ በቃችሁ መባል አለባቸው፡፡

      ባለፉት ሁለት ዓመታት በአገሪቱ ውስጥ የተቀሰቀሱ ግጭቶች ያደረሱዋቸው የንፁኃን ዕልቂት፣ የአካል ጉዳትና የሥነ ልቦና አደጋዎች አሁንም ጠባሳቸው አልሻረም፡፡ ከእነዚህም አሳዛኝ ሰቆቃዎች በፍጥነት ተወጥቶ አጠቃላይ መፍትሔ መፈለግ ሲገባ፣ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች በቅርቡ የደረሰው መቅሰፍት ያንገበግባል፡፡ ንፁኃንን በጅምላ ሰለባ ያደረገው ይህ አደጋ የአገር መከራ ነው፡፡ እንደ አገርም ሆነ እንደ ሕዝብ እጅግ የሚያሳዝንና አንገትን የሚያስደፋ መከራ ሲገጥም፣ እባካችሁ የጥፋት እጆች ይብቃችሁ መባል አለበት፡፡ የሕግ የበላይነት በአግባቡ ተከብሮ አጥፊዎች በሕግ ሲዳኙና ሥርዓት ሲኖር የጥፋት እጆች ይገታሉ፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ውስጥ መሽገው ግጭት የሚያባብሱና አገርን ለትርምስ የሚዳርጉ ኃይሎች ጥረታቸው የሚከሽፈው፣ መንግሥት ሕዝቡን በሕጉ መሠረት ብቻ ማስተዳደር ሲችል ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የሠፈሩ መብቶችን ሙሉ በሙሉ ሲያከብር ነው፡፡ አድሏዊና በሙስና የተተበተቡ ብልሹ አሠራሮችን አስወግዶ ለሕዝብ ፈቃድ ብቻ ሲገዛ ነው፡፡ ከዘመኑ አስተሳሰብ ጋር እኩል መራመድ ሲችል ነው፡፡ የወጣቱን ትውልድ ሥነ ልቦና ሲረዳ ነው፡፡ ያኔ የጥፋት እጆች ይሰበሰባሉ፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ውስጥ መሽጎ ሕዝብ ማጨራረስ ተረት ይሆናል፡፡

      ደግመን ደጋግመው እንደምንለው ለኢትዮጵያችን ህልውናና ዕድገት የሚበጀው በሕግ የበላይነት ሥር የሚተዳደር መንግሥታዊ ሥርዓት ማቆም ነው፡፡ የመላ ኢትዮጵያውያን ፈቃድ የሚፈጸመው በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ስለሆነ፣ ለዚህ የሚመጥን ቁመና ያስፈልጋል፡፡ ይህ ቁመና የሚኖረው ደግሞ ሕግ በማክበር ነው፡፡ መንግሥት ሕግ ያክብር፡፡ ዜጎችም እናክብር፡፡ የፍትሕ አካላት ሕግ ማስከበር ብቻ ሳይሆን ራሳቸውም ያክብሩ፡፡ ፓርላማው አስፈጻሚውን በመቆጣጠር ሕግ ያስከብር፡፡ ኃላፊነቱን ይወጣ፡፡ ሕገወጦች የሚፈነጩባቸው ብልሹ አሠራሮች ተጠራርገው ይወገዱ፡፡ ማኅበራዊ ፍትሕ ይስፈን፡፡ እኩልነት በተግባር ይረጋገጥ፡፡ በዚህ መሠረት መራመድ የሚያቅተው ካለ ለሕዝብ የሚጠቅም አጀንዳ አይኖረውም፡፡ ምናልባትም የጠላት ተላላኪ ወይም ቅጥረኛ ነው፡፡ ሕዝብን ከሕዝብ የማጋጨት ሱስ ያለባቸውና አገርን ካላተራመሱ መኖር የማይችሉም ከታሪካዊ ጠላቶች ተለይተው አይታዩም፡፡ ይህ ኩሩና ጀግና ሕዝብ በማስተዋል አብሮ የሚኖርና ተምሳሌታዊ የጋራ እሴቶች ያሉት ነው፡፡ ይህንን የተከበረ ሕዝባችንን ማክበርና ማገልገል ይቅደም፡፡ ለግጭት የሚያነሳሱ የጥፋት እጆች ደግሞ ይሰብሰቡ!