አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

‹‹ለስፖርቱ የምናስቀምጣቸው መሪዎች ስፖርቱ ጥላ የሚሆናቸው ሳይሆን ለስፖርቱ ጥላ የሚሆኑ ሊሆኑ ይገባል››

 

አቶ ተድላ ዳኛቸው፣ በስፖርት ማኔጅመንት የፒኤችዲ ዲግሪያቸውን በመሥራት ላይ የሚገኙ

እግር ኳስ ፌዴሬሽንን ጨምሮ 26 ብሔራዊ ፌዴሬሽኖችና አሶሴሽኖች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ሁሉም ማለት በሚያስችል መልኩ ስፖርቱ በተለይም በአሁኑ ወቅት ከደረሰበት የዕድገት ደረጃ አኳያ አደረጃጀታቸውን ጨምሮ በተለያዩ ሳንካ ተይዞ እንደሚገኝ የስፖርቱ ሙያተኞች ይናገራሉ፡፡ አቶ ተድላ ዳኛቸው በኢትዮጵያ ስፖርት በተለይም በእግር ኳስ በሙያተኝነትና በአመራርነት ከሦስት አሠርታት በላይ እንዳገለገሉ ይናገራሉ፡፡ ባለሙያው በሰውነት ማጎልመሻ ከኮተቤ መምህራን ኮሌጅ በ1977 ዓ.ም. በዲፕሎማ፣ በ1986 ዓ.ም. ደግሞ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ በሙያተኝነትና በአመራርነት በአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮና በአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን በማገልገል ላይ እያሉ በእግር ኳስ አሠልጣኝነት የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከመቐለ ዩኒቨርሲቲ በስፖርት ማኔጅመንት የፒኤችዲ ዲግሪያቸውን ‹‹ለእግር ኳስ ዕድገት በወጡ መመርያዎችና ፖሊሲዎች ተግባርና ፈተናዎች›› በሚል የመመረቂያ ጽሑፋቸውን በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያ ስፖርት ውስጥ ያለውን የስፖርት ማኔጅመንትና ተዛማጅ ችግሮች ዙሪያ ደረጀ ጠገናው አነጋግሯቸዋል፡፡ 

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ስፖርት ለበርካታ ዓመታት አገልግሎት ከሰጡ ባለሙያዎች አንዱ ነዎት፡፡ ከዚህ ባሻገር የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በእግር ኳስ አሠልጣኝነት በሁለተኛ ዲግሪ አሠልጥኖ ካስመረቃቸው ከመጀመርያዎቹ ተማሪዎችመ ይጠቀሳሉ፡፡ ይሁንና በአሠልጣኝነት ሲሳተፉ አይታዩም ምክንያቱ ምንድነው?

አቶ ዳኛቸው፡- ከልጅነቴ ጀምሮ ለእግር ኳስ የተለየ ፍቅርና ፍላጎት ነበረኝ፡፡ በተወሰነ መልኩም ቢሆን እግር ኳስ ተጫውቻለሁ፡፡ ለጎጃም ቡድን ከኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻውና አብርሃም ተክለሃይማኖት ጋር አብረን ተጫውተናል፡፡ ከዚህ ባሻገር ወደ ወሎ በማምራት ለወሎ እግር ኳስ ቡድን ተጫውቻለሁ፡፡ ወደ ዝርዝሩ ውስጥ መግባትና ማውራት ባያስፈልግም ሁለተኛ ዲግሪዬን በሠራሁበት የሙያ መስክ ብቀጥልበት ጥሩ የሥራ ድርሻ እንደሚኖረኝ አውቅ ነበር፡፡ ነገር ግን በአብዛኛው በተለያዩ የአስተዳደር ሥራዎች ውስጥ መጠመዴ የአሠልጣኝነቱነ ድርሻ ዘንግቸው ቆየሁ፡፡ የሚገርመው የካፍ ‹‹ሲ›› ላይሰንስ ሳይቀር ወስጃለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- የአሠልጣኝነት ሙያ በአካዴሚክ መታገዝ እንዳለበት እምነት ተይዞ፣ በተለይም በአሁኑ ወቅት ሁለት ዓይነት አከራካሪ ሐሳቦች ይነሳሉ፡፡ የአካዴሚክስ ዕውቀት ኖሮት በእግር ኳሱ ያላለፈ ሰው ውጤታማ መሆን እንደማይችል የሚናገሩ በአንድ በኩል በሌላ በኩል፣ ደግሞ አካዴሚክሱ አማራጭ እንደሌለው የሚያምኑ አሉ፡፡ የእርስዎ አስተያያት ምንድን ነው?

አቶ ዳኛቸው፡- የእግር ኳስ አሠልጣኝነት የራሱ የሆነ ባህሪ እንዳለው አያከራክርም፡፡ ይህንን የሙያ ክህሎት ይዞ በዕውቀት ማዳበር ደግሞ አስፈላጊ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በእግር ኳስ አሠልጣኝነት ሁለተኛ ዲግሪ መማርና ማግኘት ማለት ሙያዊ ክህሎቱ ከታከለበት ለነገ የአሠልጣኝነት ሥርዓቱ ጥሩ ፈር ቀዳጅ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በአውሮፓና መሰል አገሮች ‹‹ኮች›› ማለት ማኔጀር ነው፡፡ አሠልጣኝ የሚያወራው ስለተጨዋቾችና ስለጨዋታው እንዲሁም ታክቲክና ቴክኒክ ነው፡፡ ስለዚህ እንዴት ነው ክህሎትን ማሳደግ የሚቻለው? የሚለውን የአሠልጣኝነት ሙያ  ማስረጽና ማስገባት ይጠይቃል፡፡ ይኼ ዕውን የሚሆነወ ደግሞ ተግባሩና ንድፈ ሐሳቡ ተሟልቶ በያዙ ሙያተኞች (አሠልጣኞች) ነው፡፡ በዕውቀት ላይ ተመሥርቶ የአንድን ተጫዋች ክህሎት ለማሳደግ ዕውቀትና የሙያ ክህሎት መሠረታዊ ናቸው፡፡ ሥልጠናዎች በተለያየ ደረጃ ይሰጣሉ፡፡ የ‹‹ሲ››፣ የ‹‹ቢ›› እና የ‹‹ኤ›› የአሠልጣኝነት ደረጃዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚሰጡ ናቸው፡፡ ከእነዚህ በተጓዳኝ በረዥም ጊዜ የሚሰጡ ሥልጠናዎች ለምሳሌ በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሊሆን ይችላል የሚሰጡ ሥልጠናዎች ደግሞ ለሙያተኛው በአንድም ሆነ በሌላ አማራጭ የሌለው አቅም ማጎልበቻ ናቸው፡፡ ቀደም ሲል የገለጹት ቢሆንም እኔ በአሠልጣኝነቱ ሕይወት ውስጥ እንዳልገፋበት ካደረጉኝ ምክንያቶች ለአጭር ጊዜ የሚሰጡትን ሥልጠናዎች አለመውሰዴ ይጠቀሳል፡፡ በዘርፉ የሚንፀባረቁት ሁለት አመለካከቶች በተመለከተ፣ አንድ መምህር ወይም አሠልጣኝ ሁሉን አቀፍ የሆነ ዕውቀት ሊኖረው ይገባል፡፡ በዩኒቨርሲቲ የሰውነት ማጎልበቻ ትምህርት የሚያስተምር መምህር ለተማሪዎቹ ስለሚያስተምረው የትምህርት ዓይነት እግር ኳስ ሊሆን ይችላል ግንዛቤው ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህ ማለት ከንድፈ ሐሳቡ በተጓዳኝ ተግባራዊ እንቅስቃሴውን ጭምር የሚያውቅ ማለት ነው፡፡ ይኼ ካልሆነ በተለይ በአሠልጣኝነት የሚያስፈልገውን ሥልጠና ለሠልጣኞቹ ለመስጠት ያስቸግራል፡፡ የሚገርመው ለመጀመርያ ጊዜ በኮተቤ መምህራን ኮሌጅ (በአሁኑ ዩኒቨርሲቲ) በሰውነት ማጎልመሻ ትምህርት ክፍል ለመማር ስናመለክት፣ ዋናው የመግቢያ ፈተናው ስለምንማረው የትምህርት ዓይነት የተግባር ፈተና መውሰድ ነበር፡፡ ያንን የተግባር ፈተና ማለፍ የማይችል ተማሪ ዕድሉን አያገኝም ነበር፡፡ እኔን ጨምሮ በወቅቱ ዕድሉን ያገኘነው የተግባሩ ፈተናውን በብቃት አልፈን ነው፡፡ ቅርጫት ኳስ ለማስተማር የቅርጫት ኳስ ዕውቀት (ክህሎት) ያስፈልጋል፡፡ እግር ኳስና ሌሎችንም የስፖርት ዓይነቶች ለማስተማር በየስፖርት ዓይነቱ ዕውቀቱና ክህሎቱ ሊኖርህ ይገባል፡፡ አንድ የእግር ኳስ አሠልጣኝ ለተጨዋቹ ስለ ‹‹ድሪብሊንግ›› ራሱ ሠርቶ ማሳየት ካልቻለ በንድፈ ሐሳብ ብቻ የሚሆን አይመስለኝም፡፡ ለዚህ ትልቁና መሠረታዊ የሚባለውን ክህሎት ከልጅነት ጀምሮ ማዳበር ያስፈልጋል፡፡ የሁሉም ስፖርቶች መሠረት ጅምናስቲክ ነው፡፡ በጅምናስቲክስ ያላለፈ አሠልጣኝ ቆሞ ስለ ጅምናስቲክስ እንቅስቃሴ ንድፈ ሐሳቡን ብቻ ለተማሪዎቹ ማስተማር እችላለሁ ቢል በእኔ የውድቀት መጀመርያ ነው፡፡ ማኔጅመንትና ተግባር ለየቅል ናቸው፡፡ የትኛውም ስፖርት በተለይም በአሁኑ ወቅት ትልቅ ኢንዱስትሪ ሆኗል፡፡ ይህንን ኢንዱስትሪ ወደ ኢትዮጵየ ማምጣት የሚቻለው ደግሞ ስፖርቱ ዕውቀቱ ባላቸው መመራት ሲችል ብቻ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ በሁሉም ስፖርቶች የስፖርት ማኔጅመንቱ እንዴት ይገለጻል? 

አቶ ዳኛቸው፡- ስፖርት ከመነሻው የራሱ የሆነ አመጣጥና ታሪክ ያለው፣ ለማኅበረሰቡ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያና ፖለቲካዊ እንዲሁም በሌሎችም ሁሉን አቀፍ የሆነ ጠቀሜታና አገልግሎት የሚሰጥ ነው፡፡ ለዓለም ማኅበረሰብ አንድነትና ቁርኝት ትልቅ ድርሻ ያለው ስፖርትና ስፖርት ብቻ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ስፖርትም ከዚህ የተለየ ሊሆን አይችልም፡፡ ይሁንና የኢትያጵያ ስፖርት የተፈለገውን ያህል እየሄደ ነው? በፍፁም አይደለም፡፡ ነገር ግን ኅበረተሰቡም ሆነ መንግሥት ለስፖርቱ ሙሉ ለሙሉም ባይሆን የድርሻቸውን እየተወጡ ነው፡፡ የተሟላ ነው? አይደለም? ይኼ ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ጀምሮ አሁን እስካለው ሥርዓት ያለ ነው፡፡ ስፖርቱ እንዴት እየተመራ ነው? ሲባል ጥያቄ አለኝ፡፡ የመልካም አስተዳደር ጉድለት ይታይበታል፡፡ ሙያው እንደ ሌሎች የሙያ ተቋማት በሙያው ዕውቀቱና ብቃቱ ባላቸው ሰዎች መመራት ሲገባው ይኼ እየሆነ አይደለም፡፡ ስፖርቱ በአገሪቱ ከሚገኙ ተቋማት አንዱ ነው፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ ስፖርት አንድ ተቋም ሊኖረው የሚገባውን ያህል የሠለጠነ የሰው ኃይል አለው ወይ? ስንል የለውም፡፡ ተቋምን ተቋም የሚያሰኘው የሠለጠነ የሰው ኃይል ከሌለው በስተቀር ስሙ ብቻ ተቋም ሊያስብለው አይችልም፡፡ በዕቅድና ፕላን መመራት ሲችል ነው ተቋም ሊሆን የሚችለው፡፡ ስፖርቱ በሠለጠነ የሰው ኃይል የሚመራ ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ያስፈልገዋል፡፡ ቁጥጥርና ክትትል ያስፈልገዋል፡፡ ተከታታይና መድረሻቸውን የሚያውቅ ዕቅድ ያስፈልገዋል፡፡ የዕለት ተዕለት ብቃት ማረጋገጫ (Performances Mesurement) ያስፈልገዋል፡፡ እንደ ተቋም ተጠያቂነትና ግልጽነት ያለውና የተዘጋጀ የስፖርት ፖሊሲ ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- በ1990ዎቹ መጀመርያ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ በአገር አቀፍ ደረጃ የወጣ የስፖርት ፖሊሲ እንዳለ ይታወቃል፡፡

አቶ ዳኛቸው፡- እውነት ነው፡፡ ነገር ግን ፖሊሲውን የቀረፀው አካልና ፖሊሲውን የሚያስፈጽመው አካል ምን ያህል ተጣጥመው ፖሊሲው ዕውን ሆኗል? ፖሊሲው ከወጣ የ20 ዓመት ዕድሜ አስቆጥሯል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ስንት ጊዜ ክለሳ ተደርጎበታል? በግሌ ጥያቄ አለኝ፡፡ ምክንያቱም ፖሊሲ ማለት የራሱ የሆነ አቅጣጫና ግብም ኖሮት ሲተገበር ነው፡፡ ይኼ አልተደረገም፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ዕውቀትና ቁርጠኝነት ያስፈልጋል፡፡ ስለስፖርት ፖሊሲ የምናወራ ከሆነ የፖሊሲው ዓላማና በማስፈጸሚያ ዕቅዱ መሠረት ኅብረተሰቡ በሚኖርበት፣ በሚሠራበትና በሚማርበት ሥራ ላይ ውሎ በእንቅስቃሴ ክህሎቱና ችሎታው ያላቸውን ወጣቶች በመለየት እንዲፈጸም ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ባለው ሁኔታ በፖሊሲው የተካተቱትን ማድረግ ቀርቶ በዚህ በ20 ዓመት ጊዜ ውስጥ የፖሊሲው ወጤት (ተፅዕኖ) አልታየም፡፡ ውድቀቱን ለመገምገም ውጤቱን መገምገም ያስፈልጋል፡፡ ፖሊሲው በወጣበት ወቅት በአማራ ክልላዊ መንግሥት በስፖርቱ የመምሪያ ኃላፊ ነበርኩ፡፡ ፖሊሲ እስከ ታችኛው ክፍል ወርዶ በፖሊሲ ኔትወርክ መተሳሰር እንዳለበት አውቆ ነበር፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ አሁን ላይ እየተተገረበ ያለው እንዴት ነው? ብሎ መጠየቅና መገማገም ያስፈልጋል፡፡ የፖሊሲው ትልልቅ ባለድርሻ አካላት ከሚባት ተቋማት ትምህርት ሚኒስቴርና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፤ ነገር ግን ስፖርቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ያለው የትስስር መስተጋብር አይታወቅም፡፡ ወደ ስፖርቱ የልማት ዕቅድ (መርህ) ስንመጣ አንድ ትምህርት ቤት አንድ ቡድን ይላል፡፡ ይህን ስንቶቻችን ነን የምናውቀው? በዚህ ላይ መነጋገር፣ መተማመንና መጠያየቅም ያስፈልጋል፡፡ ስፖርት ሳይንስ ነው ስንል ይህን ሳይንስ ለመተግበር በስፖርት ማኔጅመንት ፕሮፌሽናሎችን ማሳተፍ ያስፈልጋል፡፡ መምራትም ካለባቸው ኃላፊነቱ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ በዚህ አግባብ መሄድ ካልተቻለ ለምንፈልገው መልካም አስተዳደር ጠንቅ ነው፡፡ ስለዚህ ለስፖርት መልካም አስተዳደር አንዱና የመጀመርያው የውሳኔ ሰው መሆን ይጠይቃል፡፡ ፖሊሲ አውጪዎች ፖሊሲውን ቢበዛ በየአምስት ዓመቱ መከለስ መቻል ይኖርባቸዋል፡፡ ከባለድርሻ አካላት ጋር በፖሊሲው ዙሪያ መነጋገርና መወያየት ያስፈልጋል፡፡ ፖሊሲው በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ መፈተሽ ተገቢ ነው፡፡ ባለው ሁኔታ ይህ ነገር አለ ወይ ስንል? እያንዳንዳችን ራሳችንን መመልከት ይኖርብናል፡፡ ከፍተኛ የሆነ ክፍተት አለ፡፡ 

ሪፖርተር፡- ለዚህ በዋናነት ተጠያቂ የሚሉት ይኖራል?

አቶ ዳኛቸው፡- ጠያቂና ተጠያቂ ወደ ሚለው ዝርዝር ከመግባታችን በፊት ፖሊሲ አውጪውና ፖሊሲ አስፈጻሚው መነጋገር ይኖርባቸዋል፡፡ የፖሊሲው ውጤት የጋራችን እስከሆነ ድረስ ተጠያቂነቱም የጋራ መሆን ይኖርበታል፡፡

ሪፖርተር፡- እግር ኳሱን ጨምሮ የስፖርት ተቋማት ከአገር አቀፉ የስፖርት ፖሊሲ አንፃር የሚገኙበት ደረጃ እንዴት ይታያል?

አቶ ዳኛቸው፡- ፖሊሲው ይፋ ከሆነበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ ክለሳ ተደርጎለት እንደማያውቅ እየተነጋገርን ባለበት በዚህ ሰዓት ከፖሊሲው አንፃር የፌዴሬሽኖች ቁመና እንዲህና እንዲያ ለማለት ያስቸግራል፡፡ በእርግጥ ሁሉም ተቋማት የየራሳቸው ፖሊሲ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ በየሁለት ዓመቱ ክለሳ የሚደረግለትም ሊሆን ይገባል፡፡ ይህ ባልሆነበት ትርጉም ሊኖረው አይችልም፡፡ አንድ ቦታ የተጠራቀመ ኩሬ ነው የሚሆነው፡፡ ኩሬው ወደ ተለያዩ ወንዞች እንዲፈስ የሚያደርግ ማስተንፈሻ ካልተበጀለት በሽታ አምጪ ተህዋስያን ማፍሪያ ከመሆን ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም፡፡ የምንፈልገውን ውጤት ለማግኘት የምንመራባቸው ፖሊሲዎችን መቅረፅ ብቻ ሳይሆን ወቅታዊ ክለሳም እንደሚያስፈልገው ማመን ይኖርብናል፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ በመነሳት የአገሪቱ ስፖርት ተቋማት መዋቅራዊ ተክለ ሰውነትና እንቅስቃሴ ደመነፍስ ነው ማለት እንችላለን?

አቶ ዳኛቸው፡- ስፖርቱን ለመምራት ሁለት መሠረታዊ ነገሮች ያስፈልጋሉ፡፡ የመንግሥት ወይም የድርጅት ተቀጣሪዎችና የበጎ ፈቃድ (ቮለንተርስ) አገልጋዮች አሉ፡፡ በኢትዮጵያ ባለው ሁኔታ ስንመለከት በአብዛኛው የስፖርቱን ተቋማት የሚመሩት መልካም ፈቃደኞች ናቸው፡፡ የሁለቱን አካላት ድርሻና ኃላፊነት በጥንቃቄ ማየት ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ሁለቱ ፌዴሬሽኖችንና አሶሴሽኖችን የሚመሩት አካላት ናቸው፡፡ በአገሪቱ ወደ 26 የሚጠጉ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖችና አሶሴሽኖች እንዳሉ ይታመናል፡፡ በአብዛኛው የሚመሩ በመልካም ፈቃደኛ ሙያተኞች ነው፡፡ መልካም ፈቃደኞች ለፌዴሬሽን አመራርነት እንዲመጡ ስናቅድ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለስፖርቱ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ዕውቀቱና ቁርጠኝነት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ሌላው ደግሞ የመጡበት ሁኔታና ልምዳቸው ጭምር መታየት ይኖርበታል፡፡ ወይም ደግሞ ለምናመጣቸው ሰዎች በቅድሚያ ስለሚመሩት ተቋምና ስፖርት በቂ የግንዛቤ ማስጨበጫ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ኃላፊነትና ተግባራቸው እስከምን ድረስ እንደሆነ በውል ተለይቶ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ የስፖርቱ ትልቁ ችግር ማንም ሰው፣ በፈለገው ገብቶ፣ የፈለገውን አድርጎ፣ በፈለገው ጊዜ የሚገባበትና የሚወጣበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ተጠያቂነት የለም፡፡ ይኼ በሌለበት ደግሞ ወድዬትም መንቀሳቀስ ያስቸግራል፡፡ ከዚህ ለመውጣት እያንዳንዱ የስፖርት ተቋማት በጠነከረና በተማረ የሰው ኃይል፣ ቅንና አስተዋይ በሆነ ሰው ማደራጀትና መምራት አስፈላጊ ነው፡፡ ሕግና ደንቦች ሲወጡ ለአመራርነት የሚመጡ የበጎ ፈቃድ አገልጋዮችንም የሚመለከቱ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን እያንዳንዱ ፌዴሬሽን ያለበትን ወቅታዊ አቋም አፈጻጸሙን ጭምር መገምገም መቻል ይኖርበታል፡፡ የፌዴሬሽን ጉባዔዎች በወረቀት ክምር የታጀቡ የውሸት ሪፖርቶችን ለምን? ብለው መጠየቅ የሚችሉ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ የየስፖርት ዓይነቱ ጉባዔተኛ የሚባለው አካል የስፖርቱ ትልቁ የሥልጣን አካል ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ሥልጣኑ ትርጉም ያለው ሊሆን ይገባል፡፡ በየትኛውም የስፖርት ዓይነት በእግር ኳስ፣ በአትሌቲክስ፣ በጠረጴዛ ቴኒስና በሌሎችም የምንፈልገውን ውጤት ለማምጣት ትክክለኛ የሆነ አመራር ሊሰጥ የሚችል አቅሙና ዕውቀቱ ያለው መሪ ያስፈልጋል፡፡ በሌላ መልኩ በስፖርቱ የምናስቀምጣቸው መሪዎች ስፖርቱ ጥላ የሚሆናቸው ሳይሆኑ ለስፖርቱ ጥላ የሚሆኑ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ይህን ለማድረግ ባለድርሻ አካሉና ለዚህ የሚመለከተው  የመንግሥታዊ አካሉ ቁርጠኝነት ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ ራሱ እንደየስፖርቱ ዓይነትና ባህሪ መተግበር ይኖርበታል፡፡ ስፖርቱ የአገሪቱ አንዱ የልማት አካል ነው ብለን ስንል ለዚያ የሚሆነውን ፖሊሲና ማስፈጸሚያ ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ማስቀመጥ ብቻ ሳይሆን የክትትልና ቁጥጥር ሥርዓቱንም ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንኑ በትክክል ገልጸውታል፡፡ ‹‹ስፖርቱ በሚያውቁ ሰዎች መመራት አለበት፡፡››

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ስፖርት ውስጥ ከሦስት አሠርታት በላይ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታ ቆይተዋል፣ መርተዋል፣ የስፖርቱን ወቅታዊ ደረጃ እንዴት ይገልጹታል?

አቶ ዳኛቸው፡- ስፖርት የብዙ ነገር ድምር ውጤት ነው፡፡ ይህ ማለት አሳታፊ መሆንን ይጠይቃል፡፡ ከታች ከኅብረተሰቡ ጀምሮ በእያንዳንዱ የ‹‹እኔነት›› ስሜት እንዲኖር ጠንካራ ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ ከተመለከትነው ብዙ ይቀረናል፡፡ ይኼ የመንግሥት ወይም የፌዴሬሽን ክፍተት ተድርጎ ሊወሰድ አይገባም፡፡ በየደረጃው የምንገኝ ሁላችንም ተጠያቂዎች ነን፡፡ ክለቦቻችን ማኅበረሰብ አቀፍ መሆን መቻል ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ መዋቅር ስለሌለን ነው በርካታ ክለቦቻችንን እያጣን የምንገኘው፡፡ ለእንግሊዝ እግር ኳስ ክለቦችና ሌሎች አገሮች ለዛሬው ዕድገታቸው መነሻው የገንዘብ አቅም ብቻ ሳይሆን፣ ማኅብረሰብ አቀፍ መሆናቸው ነው፡፡ በሌላውም ስፖርት ተመሳሳይ ነው፡፡                                                                       

ሪፖርተር፡- ለዚህ ተብሎ ከሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የተዋቀረ ብሔራዊ የስፖርት ምክር ቤት እንዳለ ይታወቃል፡፡ ስለ ብሔራዊ የስፖርት ምክር ቤቱ ምን ይላሉ?

አቶ ዳኛቸው፡- ነበር በሚለው እስማማለሁ፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ በውል አላውቅም፡፡ ይሁንና ይህ አገር አቀፍ ብሔራዊ የስፖርት ምክር ቤት ስፖርቱን በሚመለከት ትልቅ የሥልጣን አካል ነው፡፡ እስከማውቀው ድረስ እንደነ ዶ/ር ተቀዳ ዓለሙ፣ መላኩ ጴጥሮስና ሌሎችም በነበሩበት ጊዜ እንቅስቃሴ ሰያደርግ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ አሁን ይኑር አይኑር የማውቀው ነገር ባይኖርም ሊኖር እንደሚገባ ግን አምናለሁ፡፡ ከኅብረተሰቡ ጀምሮ በስፖርቱ የአገሪቱ ደረጃ የት ነው? ተብሎ ለሚነሳው ጥያቄ መልስ ሊያሰጥ የሚገባው ርሱ ነው፡፡ ይህ ብሔራዊ የስፖርት ምክር ቤት ከዓላማዎቹ መካከል በስፖርት ጉዳይ ላይ ሚኒስቴሩን ጭምር ያማክራል፡፡ በአገሪቱ የኦሊምፒክ ተሳትፎ ውጤት ቢጠፋ ይኼ ምክር ቤት የመገምገምና የመጠየቅ ብሎም የማኅበረሰቡን አስተያየትና ጥቆማ መነሻ በማድረግ ሊያወያይ ይችላል፡፡ የመጠየቅና የማስፈጸም ሚናም ሊኖረው እንደሚችል የተቀመጠለት የኃላፊነት ወሰን ያስረዳል፡፡ በተጨማሪም የስፖርቱ መሠረተ ልማት እንዴት ነው? የልማት ፕሮግራሞች አሉ ወይ? ፈንዶችን ሊጠቁምና ሊያመጣ የሚችልበት ሥልጣንና ኃላፊነትም አለው፡፡ ነገር ግን ይህ ምክር ቤት ለዚህ ኃላፊነት ብቁ ሆኖ እየተንቀሳቀሰ ነው የሚያስብለው ደረጃ ላይ ያለ አይመስለኝም፡፡ በአጠቃላይ  ለዚህ ደረጃ እያደረሰን ያለውን መጥፎ አስተዳደር በመልካም አስተዳደር ለመቀየር የሚያስፈልጉትን ቅድመ ሁኔታዎች ማስቀመጥና ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሳይሆን ፖሊሲውንም ሆነ መመርያውን በወረቀት ላይ ማስቀመጥ ዋጋ የለውም፡፡ የምንፈልገው ዕድገትና ለውጥ ከሆነ ቁርጠኛ አስፈጻሚና ፈጻሚ ያስፈልጋል፡፡ ስፖርቱ ወደቀ ከሚለው ውጪ ታዳጊ ወጣቶች በተለይ እንደ አዲስ አበባ በመሳሰሉ ከተሞች የማዘውተሪያ ቦታ እጥረት ላይ የሚነገር የለም፡፡ ታዳጊዎች በልማት ፕሮግራም መታቀፍ ቀርቶ እንደፈለጉ ሮጠው ስሜታቸው ያመነበትን ለማድረግ እንኳ የተገደበበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ እኔ በምኖርበት ሰሚት የሚባለው አካባቢ እሑድ እሑድ ዋናውን መንገድ ዘግተው እግር ኳስ ሲጫወቱ መመልከት እየተለመደ ነው፡፡ ምክንያቱም ይታወቃል፣ ማዘውተሪያ የለም፡፡ ነገር ግን አሁንም ውጤት እንዲያመጡልን የምንጠብቃቸው በ1989 ዓ.ም. በተዘረጋው ፕሮጀክት የተገኙትን አዳነ ግርማንና ሌሎችንም ነው፡፡ ምን እየተደረገ እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡፡ ሕዝባዊና መንግሥታዊ አካሎች የሚሠሩዋቸው ሥራዎች በውል ተለይተው አይታወቁም፡፡ መንግሥት ለሕዝባዊ አካሉ የሚሰጠው ድጋፍና መቆጣጠሪያ ሥርዓቱ አይታወቅም፡፡ ተጠያቂነት ከሌለ ውጤት እንዴት ይጠበቃል? ሊሆን አይችልም፡፡ 

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የክለብ ላይሰንሲንግ ማኔጀር ነዎት፡፡ በዚህ ረገድስ ያለው ችግር እንዴት ይገለጻል?

አቶ ዳኛቸው፡- ይኼ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የአሠራር ማዕቀፍ ነው፡፡ አስገዳጅም ነው፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 53 እንዲካተት ተደርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- የአገሪቱ ክለቦች ለካፍ የአሠራር ማዕቀፍ የሚመጥን አደረጃጀት አላቸው?

አቶ ዳኛቸው፡- በዚህ ደረጃ ባለፈው ዓመት በተለይ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች አመራሮቻቸው በተገኙበት ውይይት ተደርጓል፡፡ ከፍተኛ ሊግና ብሔራዊ ሊግም ይቀጥላል፡፡ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ያላቸውን ቁመና በተመለከተ ክለብ ላይሰንሲንግ  አምስት መሥፈርቶችን ይጠይቃል፡፡ የመጀመርያው የፖርቲንግ ክራይቴሪያ ነው፡፡ ይህም ስለወጣቶች የእግር ኳስ ልማት፣ ፍልስፍናውና ተፈላጊው በጀት ተመድቦለታል ወይ? ወጣቶቹ ሲሠለጥኑ ሐኪም፣ የሥነ ልቦና ባለሙያ፣ የሥነ ምግብና ሌሎችንም ይጠይቃል፡፡ በዚህ መሥፈርት መሠረት በክለቦቻችን ተስፋ ሰጪ ነገር አለ የተሟላ ግን አይደለም፡፡ ሁለተኛው መሠረተ ልማት ሲሆን ከግል ስታዲየም ጀምሮ እስከ 30 የሚጠጉ አስገዳጅ መሥፈርቶችን ይጠይቃል፡፡ በዚህ ረገድ በአገሪቱ በአገራችን ካለ ወልዲያ ከተማ በስተቀር የተቀሩት አያሟሉም፡፡ ሦስተኛው ፐርሶኔልና አድሚኒስትሬሽን ነው፡፡ በዚህ ላይ ክለቦቻችን የራሳቸው ጽሕፈት ቤት ያላቸው አሉ፡፡ በጥገኝነት ያሉም አሉ፡፡ በዚህ መሥፈርት ውስጥ ክለቦች ማኔጀር፣ ፋይናንስና ሌሎችም ዲፓርትመንቶች እንደሚያስፈልጋቸው ያሰገድዳል፡፡ አራተኛው ፋይናንሻል መሥፈርት ነው፡፡ ክለቦች የራሳቸውን አሴት ጨምሮ የሚያወጡት ዓመታዊ በጀትና ወጪን ጭምር የሚያሳይ የአሠራር ሥርዓት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ የሚቀር ነገር አለ፡፡ ፌዴሬሽኑ ራሱ የክለቦችን የፋይናንስ ሪፖርት በተወሰነ ጊዜ ማየትና መመርመር እንዳለበት መሥፈርቱን ያስገድዳል፡፡ የሌሎች አገሮች ተሞክሮ የሚያሳየው ይህንኑ ነው፡፡ አምስተኛ ሌጋል ክራይቴሪያ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ክለቦቻችን ዕውቅና አላቸው፡፡ በካፍ የአይቲ ፕሮግራም ውስጥም ገብተዋል፡፡