አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

‹‹ድህነትን በመቀነስ የኢትዮጵያውያንን ሕይወት ለማሻሻል የሚረዱ አካታች ፕሮግራሞችን ተግባራዊ ለማድረግ ጥረቶች እየተደረጉ ነው››

 

አቶ ሀዲስ ደስታ ታደሰ፣ የቢልና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን የኢትዮጵያና የአፍሪካ ኅብረት ዳይሬክተር

አቶ ሀዲስ ደስታ ታደሰ የቢልና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን የኢትዮጵያና የአፍሪካ ኅብረት ዳይሬክተር በመሆን በቀጣናው ፋውንዴሽኑ አጋርነቱን እንዲያስፋፋ፣ በኢትዮጵያም በግብርናው መስክ፣ በጤና፣ በፋይናንስ፣ በውኃና ሳኒቴሽን፣ በተመጣጠነ ሥነ ምግብ፣ በድንገተኛ ዕርዳታ መስክ ኢንቨስት ከማድረግ ባሻገር የዲፕሎማሲ ግንኙነቶችን በመፍጠር ከአፍሪካ ኅብረት፣ ከአውሮፓ ኅብረት፣ ከሌሎች ቁልፍ ባለድርሻዎች፣ ከመንግሥታት፣ ከግሉ ዘርፍ፣ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶችና ከመሳሰሉት ጋር ፋውንዴሽኑ ያሉትን ግንኙነቶች ይመራሉ፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2007 ጀምሮ ፋውንዴሽኑን ተቀላቅለው በመሥራት ላይ የሚገኙት አቶ ሀዲስ፣ ከመንግሥት ጋር የሚደረጉ ግንኙነቶችን ከሲያትል ከተማ በመሆን ጭምር ሲመሩ ቆይተዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2012 ወደ ኢትዮጵያ በመምጣትም የቢልና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን የኢትዮጵያ ጽሕፈት ቤትን መሥርተዋል፡፡ የጌትስ ፋውንዴሽንን ከመቀላቀላቸው በፊት በሲያትል የዋሽንግተን ከንቲባ ለነበሩት ግሬግ ኒክለስ ከፍተኛ የፖሊሲ ጉዳዮች አማካሪ በመሆን፣ ከንቲባውንና ካቢኔያቸውን ከተማ ነክ በሆኑ ፖሊሲዎች፣ በኅብረተሰብ ጤና፣ በቤቶችና በሲቪል መብቶች ሲማክሩ ቆይተዋል፡፡ በአሜሪካ የሚኖሩ የሌሎች አገሮች ዜጎችንና ስደተኞችን ጉዳይ የሚመለከተውን ክፍል በመምራት እነዚህን ማኅበሰረቦች ለመደገፍ የሚረዱ አዳዲስ አሠራሮችን አስተግብረዋል፡፡ በትልውድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት አሜሪካዊ የሆኑት አቶ ሀዲስ፣ ከ25 ዓመታት በላይ በአሜሪካ በመኖርና በማገልገል ሰፊ ልምድ አካብተዋል፡፡ በፐብሊክ አድሚኒስትሬሽን የማስተርስ ዲግሪያቸውን ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ዋሺንግተን ተቀብለዋል፡፡ በበርካታ ተቋማት ውስጥ በቦርድ አመራርነት ያገለገሉት አቶ ሀዲስ፣ የጀርመን ማርሻል ፈንድ የተባለውንና ለአሜሪካና ለአውሮፓ ኅብረት የሚውለውን ፌሎሺፕ ጨምሮ በሌሎችም በርካታ መድረኮች ተሳትፈዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ፋውንዴሽኑ ዓለም አቀፍ ሪፖርት ማውጣቱን ተንተርሶ፣ ሁለቱ የዓለም ቢሊየነሮችና ለጋሾች በኢትዮጵያና በተቀረውም ዓለም ስለሚከናውኗቸው ልማት አገዝ ድጋፎችና ሌሎችም ጉዳዮች ብርሃኑ ፈቃደ ከአቶ ሀዲስ ታደሰ ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡   

ሪፖርተር፡- ቢልና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ይፋ ያደረገው ዓለም አቀፍ ሪፖርት በጤና፣ በትምህርት እንዲሁም በግብርናና በሌሎችም መስኮች የተገኙ ውጤቶችንና ያጋጠሙ ፈተናዎችን ከሥጋቶች፣ ብሎም ካለፉት የሚሌኒየሙ ግቦችና በአሁኑ ወቅት እየተተገበሩ ከሚገኙ የዘላቂ ልማት ግቦች አኳያ ሪፖርቱ ስለሚያትታቸው ነጥቦች በመጠኑ ቢገልጹልን?

አቶ ሀዲስ፡- 193 አገሮች የዘላቂ ልማት ግቦችን እ.ኤ.አ. በ2030 ለመተግበርና ለማሳካት ቃል መግባታቸው ይታወቃል፡፡ ይፋ በተደረገው ሪፖርትም (‹‹ጎልኪፐርስ›› በሚል ርዕስ) በዓለም ዙሪያ እስካሁን የተገኙ ውጤቶችን ለማሳየት ሞክረናል፡፡ የምንገኝበት ወቅት በጣም ፈታኝ ነው፡፡ በመሆኑም የሚታዩትን ጉድለቶችም ለማመላከት ሞክረናል፡፡ አንዳንዶቹ ጉድለቶች የሚመነጩት ከዓለም የፋይናንስ ቀውስ ጋር በተያያዘ ሲሆን፣ አንዳንድ በአሜሪካና በአውሮፓ የሚገኙ አገሮች የፋይናንስ ችግር ስላጋጠማቸው የበጀት ቅነሳ ሲያደርጉ ይታያሉ፡፡ በሪፖርቱ ወደፊት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ክስተቶችን ለመጠቆም ጭምር ጥረት አድርገናል፡፡ እስካሁን ስናከናውን የቆየናቸውን ኢንቨስትመንቶች በዚያው አግባብ ማስቀጠል ካልቻልን፣ የብዙዎች ሕይወት አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡ ሪፖርቱ በጥሩና በመጥፎ አኳኋን ሊያጋጥሙ የሚችሉ ዕድሎችን ለመተንበይ ሞክሯል፡፡ እስካሁን የተገኙትን ውጤቶች ማስጠበቅና በዚያው መጠን መቀጠል ከተቻለ የሰዎች ሕይወት እንዴት ሊሻሻል እንደሚችል ያሳያል፡፡ በአንፃሩ የለውጥ ውጤቶቹን የሚገቱ አካሄዶች የሚመጡ ከሆነ ግን በርካታ ሰዎች አደጋ ውስጥ ሊወድቁ እንደሚችሉም ይጠቁማል፡፡ በሪፖርቱ በርካታ መሪዎች በዓለም ዙሪያ ስላከናወኗቸው ተግባራትም ተተንትኗል፡፡ በመሆኑም ከዚህ ዓመት ጀምሮ እ.ኤ.አ. እስከ 2030 ድረስ ይህ ሪፖርት በየዓመቱ እንዲወጣ እናደርጋለን፡፡ በዚህ መሠረት የታዩ ለውጦችን፣ ፈታኝ ጉዳዮችንና ክፍተቶችን እያሳየን መንግሥታት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ለማድረግና የተቀመጡት ግቦች እንዲሳኩ ለማገዝ ሪፖርቱ በየዓመቱ መውጣት ይጀምራል፡፡

ሪፖርተር፡- የሚሌኒየሙ የልማት ግቦች የሚጠበቀውን ያህል ሳያሳኩ ተደምድመዋል፡፡ ግቦቹ ያልተሳኩበት አንደኛው ምክንያት የፋይናንስ እጥረት እንደነበር እዚህ በተካሄደው ፋይናንስ ለልማት ጉባዔ ወቅት ተጠቅሷል፡፡ በርካታ ትሪሊዮን ዶላሮች እንደሚያስፈልጉ ቢታወቅም፣ ያደጉ አገሮች ግን ከእንዲህ ዓይነቱ  የድጋፍ ጥሪ እየሸሹ ይገኛሉ፡፡ የእዚህን አሳሳቢነት እንዴት ይመለከቱታል?

አቶ ሀዲስ፡- በዚህ ጉዳይ ላይ ከፍተኛ ሥጋት አለን፡፡ ለዚህም ጭምር ነው በዚህ ወሳኝ ወቅት ይህንን ሪፖርት ያወጣነው፡፡ በሪፖርቱ ከተካተቱት ውስጥ አንድ ጥሩ ምሳሌ ላንሳ፡፡ እስካሁን ድረስ በኤችአይቪ ምክንያት 35 ሚሊዮን ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል፡፡ ይህም በዓለም ላይ ከታዩ አስከፊ የሰብዓዊ ቀውሶች ውስጥ አንዱ እንዲሆን  አድርጎታል፡፡ ቀላል ጉዳይ አይደለም፡፡ ተጨማሪ 36 ሚሊዮን ሰዎች ከኤችአይቪ/ኤድስ ጋር ይኖራሉ፡፡ ትንታኔያችን እንደሚያመላክተው ከሆነ ለኤችአይቪ/ኤድስ ከሚውለው ድጋፍ የአሥር በመቶ ፈንድ ቅናሽ ቢደረግ፣ 5.6 ሚሊዮን ሰዎች እ.ኤ.አ. እስከ 2030 ሊሞቱ እንደሚችሉ ነው፡፡ በመሆኑም አነስተኛ የገንዘብ ድጋፍ ቢቀነስ መጥፎ ጉዳት ሊደርስ እንዲሚችል ያሳያል፡፡ ይህንን ከእናቶች ጤና፣ ከሕፃናት ጤና፣ ከሥነ ምግብና እንደ ቲቢና ወባ ካሉት በሽታዎች ጋር ስታዛምደው ምን ያህል ሰዎች ሊጎዱ እንደሚችሉ መገመት አያዳግትም፡፡ ለዚህም ነው ይህ ሪፖርት መልካም አጋጣሚዎችንና ፈታኝ ሁኔታዎችን እንዲያመላክት በማሰብ የተዘጋጀው፡፡ የኤችአይቪ ሥርጭትን ለመቀነስ ያስቻሉ ትልልቅ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ ይሁንና አሁን የድጋፍ ፈንድ የምናቆምበት ጊዜ አይደለም፡፡ እኛ እንደምናምነው ከሆነ እስካሁን የተገኙትን ውጤቶች ይበልጥ አጠንክሮ ለመቀጠልና በሰዎች ሕይወት ውስጥ ለውጥ ለማምጣት የሚያስፈልግበት ጊዜ ቢኖር አሁን ነው፡፡ ይህ ለእኛ የሞትና የሕይወት ጉዳይ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ከኤችአይቪ በተጨማሪ ረሃብም ሌላኛው አሳሳቢ ክስተት ነው፡፡ በሪፖርቱ ስለዚህ ጉዳይ የተባለ ነገር አለ?

አቶ ሀዲስ፡- ግብርና ከሌሎቹ ተለይቶ አይታይም፡፡ በዘርፉ ሲደረግ ከነበረውም በላይ ከባድ ኢንቨስትመንት ማካሄድ ይኖርብናል፡፡ ይሁንና በግብርና ዘርፍ ውስጥ የተለመዱት መደበኛ ፈተናዎች ብቻም ሳይሆኑ እንደ አየር ንብረት ለውጥ ያሉ ለመገመት የሚያዳግቱ፣ ተፅዕኗቸውም በየጊዜው ተለዋዋጭ እየሆነ የመጡ ፈታኝ ችግሮችም አብረውት ይነሳሉ፡፡ ከዚህ በመነሳት ብዙ ኢንቨስት ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ ገበሬዎች የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችሉበት፣ ጥሩ የምርጥ ዘር ሥርጭት የሚከናወንበት ብቻም ሳይሆን የማዳበሪያና የገበያ ዕድል ስለመመቻቸቱ እርግጠኛ መሆንንም ያካትታል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም በግብርናው መስክና በእንስሳት ዘርፍ የምናደርገውን ኢንቨስትመንት እየጨመርን እንገኛለን፡፡ ይህን ስናደርግ ሌሎችም ተበረታትተው ተመሳሳዩን እንዲያከናውኑ በማሰብ ጭምር ነው ኢንቨስትመንታችንን የምናሳድገው፡፡

ሪፖርተር፡- የዘላቂ ልማት ግቦች መተግበር ከጀመሩ ሁለተኛ ዓመታቸውን አስቆጥረዋል፡፡ በትግበራ ወቅት የሚታዩት ምልክቶች ስለወደፊቱ ምን ያመላክታሉ? አገሮች የሚያስፈልጋቸውን ፋይናንስና ሌሎች ድጋፎችን እያገኙ ነው?

አቶ ሀዲስ፡- ጥያቄውን ከአገሮች ሁኔታ አኳያ ማየት ያስፈልጋል፡፡ የትኛው አገር ምን እየሠራ ነው፣ መቼ እና የመሳሰሉትን ጥያቄዎችን ማየት ይገባል፡፡ ከዚህ አኳያ ለሁሉም የሚሆን አንድ ዓይነት ምላሽ መስጠት ይከብዳል፡፡ አንዳንድ አገሮች በሚገባ ተዘጋጅተውና ትኩረት ሰጥተው ሲሠሩ ይታያሉ፡፡ ኢትዮጵያን ከእነዚህ አገሮች ተርታ እመድባታለሁ፡፡ የአገሪቱ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ብሔራዊ ዕቅድ ለሁሉም ዘላቂ የልማት ግቦች ትኩረት ይሰጣል፡፡ በተለያዩ የልማት አውታሮች ውስጥ የሚካሄደው ኢንቨስትመንት አመርቂ ነው፡፡ በሌላ በኩል እንደ ኢትዮጵያ ዓይነት የኢንቨስትመንት መጠንና ትኩረት የማይሰጡ አገሮችም አሉ፡፡ የለጋሾች ሚናም የሚጠቀስ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ለጋሾች ዘላቂ የልማት ግቦቹ እንዲሳኩ ቁርጠኛ ድጋፍ ይሰጣሉ፡፡ በአንፃሩ ሌሎች ደግሞ ለታዳጊ አገሮች ሲሰጡ የነበረውን ድጋፍ እየቀነሱ መጥተዋል፡፡ በእርግጥ የራሳቸውን ከባድ ችግር ለመፍታት የሚታገሉ አገሮች አሉ፡፡ በጦርነት መሀል አሊያም በከባድ ብሔራዊ አደጋ ውስጥ ከገቡ ለልማት ግቦች የሚሰጡት ትኩረትና የሚያቀርቡት ሀብት አቅጣጫውን መቀየሩ የማይቀር ነው፡፡

ሪፖርተር፡-  ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን ምን ያህል እንደሆነ በሪፖርቱ ተካቷል?

አቶ ሀዲስ፡- እርግጥ በሪፖርቱ ባይጠቅስም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ዘላቂ የልማት ግቦችን በሚነድፍበት ወቅት፣ ከአዲስ አበባው ፋይናንስ ለልማት ጉባዔ ወቅት፣ በየዘርፉ ለሚያስፈልጉ ተግባራትና እንደየአገሮቹ ተጨባጭ ሁኔታ የሚያስፈልገውን የገንዘብ መጠን  አስታውቆ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ልማት ተኮር ለሆኑ ተግባራት የራሷን በጀት ትመድባለች፡፡ ለጋሾችም የሚያደርጉት ዕገዛ ቀላል አይደለም፡፡ በፋይናንስ ረገድ የሚያስፈልገው መጠን ምን ያህል እንደሆነ በግልጽ መቀመጡም አንዱና ዋናው ቁም ነገር ነው፡፡ ይሁንና ከአፍሪካ አገሮችና ከለጋሾች የሚፈለገው ገንዘብ ሥራ ላይ ለማዋል በሚፈለግበት ወቅት ስለመገኘቱ ነው የምንነጋገረው፡፡

ሪፖርተር፡- በኦፊሴላዊ የልማት ትብብር ስም ወይም በሌሎች መንገዶች ድጋፍ ሲያደርጉ የቆዩ አገሮች በአሁኑ ወቅት ወደ አገር ውስጥ ምንጮች እንዲያዘነብሉ ተቀባይ አገሮችን እየወተወቱ ይገኛሉ፡፡ ሪፖርቱ እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን ያየበት አግባብ ይኖር ይሆን?

አቶ ሀዲስ፡- ሪፖርቱ ስለዚህ ጉዳይ የሚለው ነገር አለው፡፡ አቋማችንም ቀጥተኛ ነው፡፡ ኦፊሴላዊው ዕርዳታ ወይም የአገር ውስጥ ሀብት ብቻውን ምንም አይፈይድም፡፡ ነገር ግን የሁለቱ ጥምረት ነው ለልማት የሚፈለገው፡፡

ሪፖርተር፡- ቢልና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን በበርካታ አገሮች ውስጥ ተጎጂ ለሆኑ ማኅበረሰቦች ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ይሁንና በኢትዮጵያ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መከካል ያሳካቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?

አቶ ሀዲስ፡- አጋርነታችንን በማጎልበትና በማጠናከር ላይ እናተኩራለን፡፡ ምክንያቱም ኢንቨስት በምናደርግባቸው አገሮች ውስጥ አንደኛው ጥንካሬያችን ስትራቴጂካዊ አጋርነት መፍጠር መቻላችን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥት ለሚቀርፃቸው የኢኮኖሚ ሞዴሎች የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ማማከሩ ጥንካሬው ነው፡፡ በጤና መስክ በተለይም ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ከሌሎች ለጋሾች ጋር በመሆን በጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች ፕሮግራም መስክ ለኅብረተሰቡ በሚቀርበው አገልግሎት ምክንያት የጤና ውጤቶች ተሻሽለዋል፡፡ አገሪቱም የሚሌኒየሙን የልማት ግቦች ማሳካት ችላለች፡፡ በግብርናውም መስክ ኢንቨስት እናደርጋለን፡፡ ዘርፉ ለኢትዮጵያ ተስፋ ከሚጣልባቸው የኢኮኖሚ ሀብት ምንጮች ዋናው ነው፡፡ በግብርናው መስክ የምንሠራው ሥራ ስትራቴጂካዊ ሲሆን፣ ከእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ጋር በአጋርነት በመሥራት በተለይ የአነስተኛ ገበሬዎችን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ድጋፍ እናደርጋለን፡፡ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲን መመሥረት ከምንሰጣቸው ድጋፎች መካከል በጉልህ የሚጠቀስ ነው፡፡ ኤጀንሲው የመንግሥትን የግርብርና ትራንስፎርሜሽን አጀንዳዎች ለማስፈጸም የሚያግዝ ተቋም ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ፋውንዴሽኑ በኢትዮጵያ በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎቹ ውስጥ ፈታኝ የሆኑበት ጉዳዮች ምንድን ናቸው?

አቶ ሀዲስ፡- ያጋጠመን ፈተና በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌላውም አገር ሊያጋጥም የሚችል ነው፡፡ ችግሩ በተጨባጭ በሚታየው ከፍተኛ ፍላጎትና ፍላጎቱን ለማሟላት በሚያስፈልገው ነገር መካከል ያለው አለመጣጣም ነው፡፡ ሌሎችም ከግብርናና ከጤና ዘርፎች ውጪ ያሉ በርካታ የልማት ፈተናዎች እንዳሉ እንገነዘባለን፡፡ ሁሉንም ነገር እኛ ብቻ ልንወጣው አንችልም፡፡ ቁልፍ ከሆኑ ተዋናዮችም አስፈላውጊው ፈርጀ ብዙ ሀብት አካተን ችግሩን ለማስወገድ እየታገልን ነው፡፡ ከለጋሾችና ከመንግሥት ጋር በመተባበር ድህነትን በመቀነስ የኢትዮጵያውያንን ሕይወት ለማሻሻል የሚረዱ አካታች ፕሮግራሞችን ተግባራዊ ለማድረግ ጥረቶች እየተደረጉ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከግብርናና ከጤና ባሻገር ፋውንዴሽኑ በሌሎችም መስኮች ላይ ትኩረት ያደርጋል፡፡ ሁለቱ ጥንዶችም በለጋስነታቸው በርካታ የተቸገሩ ሰዎችን ለመደገፍ እየሞክሩ ነው፡፡ በዚህ መስክ ያሉ እንቅስቃሴዎችን ቢጠቅሱልን?

አቶ ሀዲስ፡- ከግብርናና ከጤና ባሻገር ፋውንዴሽኑ አስከፊ ድህነትን ከዓለም ለማስወገድና ይህንንም ተግባር የሚደግፉ ጥረቶችን በመደገፍ በድሆች አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ሕዝቦች ሕይወታቸው ተሻሽሎ፣ በዓለም አካታች የፋይናንስ ሥርዓት ውስጥ እንዲሳተፉ ለማድረግ እየጣርን ነው፡፡ በአጭሩ መሠረታዊ የፋይናንስ አገልግሎቶች ሲኖሩ፣ ድሆች በሚያኙት ገንዘብ ሕይወታቸውን ለማሻሻል ጥቅም ላይ ያውሉታል፡፡ በመሆኑም ከመደበኛው የፋይናንስ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ተነጥለው የሚገኙ ሰዎች የባንክ ሒሳብ እንዲኖራቸው፣ የብድርና የመድን አገልግሎቶችን ማግኘት እንዲችሉ ፋውንዴሽኑ ይጥራል፡፡ ምንም እንኳ ድሆችን በዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓት ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ ሁሉንም እንቅፋቶች ይቀርፋል ባንልም፣ ነገር ግን ከድህነት ለመውጣት አንዱ ዕርምጃ መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ ዛሬ በሞባይል ስልክ አማካይነት ለሰዎች የፋይናንስ አገልግሎቶች ማግኘት ቀላልና ብዙ ወጪ የማይጠይቅ ሆኗል፡፡ አዎንታዊ ተፅዕኖውንም ማየት ጀምረናል፡፡ የባንክ ሒሳብ ያላቸው ሰዎች ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ መጥቷል፡፡ ይህ ዓይነቱ የፋይናንስ አገልግሎት በተለይ ለሴቶች ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ ምክንያቱም በአብዛኛው ሴቶች ኢኮኖሚያዊ ውሳኔዎች ላይ ከተሳትፎ ውጪ ሆነው ስለቆዩ ለውጡ በእነሱ ላይ የሚያመጣው ተፅዕኖ ለየት ይላል፡፡

ሪፖርተር፡- የፋውንዴሽኑ እንቅስቃሴዎች በመንግሥት ዓይን እንዴት ይታያሉ?  ፋውንዴሽኑ ከሲቪል ማኅበረሰቡ ጋር በሚያደርገው ግንኙነት የባለሥልጣናቱ ዕይታስ ምን ይመስላል?

አቶ ሀዲስ፡- በኢትዮጵያ አንዱ ቁልፍ አጋራችን መንግሥት ነው፡፡ በጤናውም ሆነ በግብርናው መስክ የምናከናውናቸው ሥራዎች ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ከእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ጋር በቅርበት ተባብረን የምንተገበራቸው ናቸው፡፡ ስትራቴጂያችንም ከጤና ጥበቃ ሥራዎችና ከግብርና ምርታማነት አኳያ በብሔራዊ ደረጃ ከተነደፉ የልማት ግቦች ጋር የሚጣጣም ነው፡፡ መንግሥት ቅድሚያ በሚሰጣቸው ጉዳዮች ላይ መግባባት እንዲኖረን ሳናቋርጥ እየሠራን ነው፡፡ በዚህም በየትኛው መስክ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባን እንለያለን፡፡ ከዩኒቨርሲቲዎች፣ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች፣ ከግሉ ዘርፍ፣ ከሚዲያውና ከሌሎችም ተዋናዮች ጋር አብረን እንሠራለን፡፡ ትብብሩን ባጠናከርን ቁጥር፣ ውጤቶቹና መልካም ተፅዕኖዎቹም የዚያኑ ያህል መልካም ይሆናሉ፡፡  

ሪፖርተር፡- ከቀናት በፊት ይፋ በተደረገው ሪፖርት የሕፃናትና የእናቶች ሞት መጠን መቀነስ እንደተቻለ ተዘርዝሯል፡፡ ከሕፃናት ሞት አኳያ ሲታይ በእናቶች ሞት ቅነሳ ላይ በኢትዮጵያ የሚታየው ለውጥ ግን አሁንም ከባድ ነው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያቱ ምንድነው?

አቶ ሀዲስ፡- ካስመዘገብነው አመርቂ ውጤት ባሻገር የእናቶች ሞት ግን ቤተሰቦችንና ማኅበረሰቦችን ማናጋቱን ቀጥሏል፡፡ በዓለም ላይ በእርግዝና ወቅት አሊያም በወሊድ ጊዜ የሚሞቱ እናቶች ቁጥር በግማሽ የቀነሰው በአብዛኛው በጤና ላይ በተለይም እናቶች በቤት ከመውለድ ይልቅ በጤና ተቋማት እንዲወልዱ ለማስቻል ኢንቨስት ባደረጉ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ውስጥ ትልቅ ለውጥ ታይቷል፡፡ ለእናቶች ሞት መንስዔ የሆኑትን አብዛኞቹን ነገሮች መከላከል ይቻላል፡፡ ይሁንና የእናቶችን ሕይወት መታደግ እንደሚቻል ብናውቅም እንኳ አብዛኞቹ ሥራዎች ወደ እነዚህ እናቶች ሲሄዱ አይታዩም፡፡ ይህም ለከፍተኛ የእናቶች ሞት በከፍተኛ ደረጃ መጨመር አንዱ መንስዔ ነው፡፡ ከቤት ይልቅ በጤና ተቋማት የሚወልዱ እናቶችና ልጆቻቸው በየጤና ተቋማቱ የሚያገኙት የክብካቤ ጥራት አለመሻሻልም ሌላኛው ለእናቶች ሞት መጨመር ሰበብ ነው፡፡ በኢትዮጵያ በተለይ የጤና ኤክስቴንሽን ሥርዓት ከተመሠረተ ከአሥር ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ ሥርዓቱ ከላይ ወደ ታችና ከታች ወደ ላይ የሚደረጉ ጥረቶችን የሚደግፍ በመሆኑም፣ ውጤታማ የእናቶችና የሕፃናት ሞት ቅነሳ እንዲመዘገብ አስችሏል፡፡ በኢትዮጵያ በቤት ውስጥ ከመውለድ ይልቅ በየጤና ተቋማቱ በመውለድ በኩል ትልቅ እመርታ ተመዝግቧል፡፡ ይሁንና በዚህ በኩል የተመዘገበው ለውጥ ላይ ፈታኝ ሁኔታዎች ይታያሉ፡፡ አብዛኞቹ ተቋማት በእርግዝናና በወሊድ ወቅት የሚሰጡ ጥራት ያላቸው አገልግሎቶችን አላሟሉም፡፡ በዚህ ሳቢያ በወሊድ ጊዜ እንዲሁም ከወሊድ በኋላ ባሉት ወሳኝ የ48 ሰዓታት ጊዜያት ውስጥ እናቶች እንዳይሞቱ ለማድረግ ሙሉ በሙሉ አልተቻለም፡፡ እንደ ፋውንዴሽኑ ከሆነ ግንዛቤው ያለውና እንዲበቃ የተደረገ ማኅበረሰብ ወቅቱን የጠበቀ፣ ምላሽ የሚሰጥ፣ ተመጣጣኝና ከፍተኛ ጥራት ያለው አገልግሎት ስለማግኘቱ ራሱንም ሥርዓቱንም ተጠያቂ ማድረግ እንደሚችል እምነታችን ነው፡፡ ይህ እምነታችን በጤና ክብካቤ መስክ የምናደርገውን ኢንቨስትመንት አጠናክረን እንድንቀጥል የሚያነሳሳን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከተመጣጠነ የሥነ ምግብ ፍላጎት አኳያ፣ ከአምስት ዓመት በታች ያሉና የሚቀነጭሩ ሕፃናትን በሚመለከት ስለኢትዮጵያ ምን ሊባል ይችላል?

አቶ ሀዲስ፡- በዓለም ደረጃ 45 በመቶው ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ሕፃናት የሚሞቱት በተመጣጠነ ምግብ ማነስ ነው፡፡ ተመጣጣኝ ምግብ ማግኘት ያልቻለ ሕጻን፣ በሽታ የመቋቋም አቅሙ የተዳከመ ሲሆን፣ ሕፃኑ በሽታ እንዲፀናበት፣ አስከፊ እንዲሆንበትና የበሽታው የቆይታ ጊዜም እንዲራዘምበት ምክንያት እየሆነ ነው፡፡ ቅንጭርነት ያለበት ሕፃን ከሌለበት ሕፃን ጋር ሲወዳደር የመሞት ዕድሉ ከአምስት እጅ በላይ ነው፡፡ ምንም እንኳ በኢትዮጵያ ለውጦች ቢመዘገቡም፣ ብዙ መሥራት  ይጠበቃል፡፡ ቅንጭርነት የሚያጠቃቸው ሕፃናት ቁጥር 38 በመቶ ናቸው፡፡ ከግማሽ በመቶ በላይ ሕፃናት ደካማ አቅም ያላቸው ሲሆኑ፣ ሰባት በመቶ የሚሆኑት ሕፃናት ደግሞ በዝቅተኛ ደረጃ ተቀባይነት ካገኘው የአመጋገብ ሥርዓት በታች ምግብ የሚያገኙ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ከሚታዩባቸው በርካታ ችግሮች ባሻገር እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ጥቂት አገሮች የሚሌኒየሙን የልማት ግቦች ያሳኩ ተብለዋል፡፡ ፋውንዴሽኑ የተሳኩና ያልተሳኩ ግቦች የትኞቹ እንደሆኑ ገምግሟል?

አቶ ሀዲስ፡- የሚሌኒየሙ የልማት ግቦች በተለያዩ መስኮች ዓለም አቀፍ ስኬት እንዲመዘገብ ምክንያት ሆነዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1990 ከአምስት ዓመት በታች ከሆኑ ሕፃናት መካከል በቀላሉ መከላከል በሚቻሉ ችግሮች ምክንያት በየዓመቱ 12 ሚሊዮን ሕፃናት ይሞቱ ነበር፡፡ ይህም ማለት አምስተኛ ዓመት ላይ መድረስ ከሚችሉት ከአምስቱ አንዱ ይሞት ነበር ማለት ነው፡፡ ይሁንና ይህ ቁጥር እ.ኤ.አ. በ2016 ወደ አምስት ሚሊዮን ዝቅ ብሏል፡፡ ለዚህ ስኬት ጠንካራ ዓለም አቀፋዊና አገራዊ የክትባት ዘመቻዎች ቁልፍ ሚና ነበራቸው፡፡ በመላው ዓለም የነበረው የአስከፊ ድህነት መጠንም እ.ኤ.አ. ከ1990 እስከ 2010 ባለው ጊዜ ውስጥ (ከተቀመጠው ጊዜ ገደብ በአምስት ዓመት ቀድሞ ተሳክቷል) በግማሽ ቀንሷል፡፡ ኤድስም ከአሥር ዓመታት በፊት እንደነበረው አስከፊ መፍትሔ የለሽ በሽታ መሆኑ አክትሟል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከአሥር ሚሊዮን በላይ ሰዎች የፀረ-ኤችአይቪ/ኤድስ ሕክምና ማግኘት ችለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የሚጠይቀው ወጪም በፊት ከነበረው በ99 በመቶ ቀንሷል፡፡ በኤችአይቪ የመለከፍ ቁጥርም በአንድ ሦስተኛ ቀንሷል፡፡ በቲቢ በሽታ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርም በ50 በመቶ ቀንሷል፡፡ ከአሥር ዓመታት በፊት ዓለም እንዲህ ያሉ በሽታዎችን ለመዋጋት የሚያስችላት ጥሩ ሥልት አልነበራትም፡፡ አሁን ግን ዕቅዶቹ፣ አጋርነቶቹና ውጊያውን ለማሸነፍ የሚያስችሉ ዘዴዎች አሉን፡፡ ምንም እንኳ ግቦቹን ሙሉ ለሙሉ ማሳካት ባይቻልም፣ ዓለም አቀፍ ትኩረት መፈጠሩ ትልቅ ለውጥ እንዲመዘገብ አስችሏል፡፡ አብዛኛው ለውጥ የተመዘገበውም በአፍሪካ ነው፡፡ በሚሌኒየም የልማት ግቦች ረገድ ስኬት ካስመዘገቡ 20 ታዳጊ አገሮች ውስጥ 11 አገሮች በአፍሪካ የሚገኙ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ምንም እንኳ የኤችአይቪ/ኤድስ ሥርጭት ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ አገሮች ውስጥ ትርጉም ያለው ቅነሳ ቢያሳይም መልሶ እያንሰራራ ነው፡፡ ለዚህ ችግሩ ምንድን ነው?

አቶ ሀዲስ፡- ቀደም ብለን እንደተነጋገርነው፣ ባለፉት 15 ዓመታት ውስጥ በነበሩ ፀረ ኤችአይቪ/ኤድስ ዘመቻዎች ውስጥ በርካታ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ ሆኖም መንግሥታት ትኩረታቸውን ወደ ሌሎች ጉዳዮች በማዞራቸው ይህ ስኬት ሥጋት ውስጥ ሊወድቅ ችሏል፡፡ በቀላሉ ለማየት እንደሚቻለው የበጀት ቅነሳ እየተደረገ መሆኑ ለኤድስ የሚሰጡ ምላሾችን ፈተና ውስጥ በመክተት በርከቶች እንዲሞቱ ሰበብ እየሆነ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ፀረ ኤድስ ምላሾች እንዲጠናከሩ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ ማለት በጥቂቱ ለአገልግሎት፣ ለምርምርና ልማት፣ ለኤችአይቪ ውጤታማ ሕክምናዎችን የመለየትና የመከላከል ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠል መቻል ማለት ነው፡፡ ይህ ባልተደረገበት ሁኔታ የኤድስ ሥርጭትን በቀላሉ ለመግታት የሚረዱ አዳዲስ ግኝቶችን ማምጣት አይቻልም፡፡ በእጃችን ውስጥ የሚገኙ ሥልቶችን ለመቀጠም ኢንቨስት የማናደርግና ለሕክምና ወጪ የማናደርግ ከሆነ በርካቶች መሞታቸው አይቀሬ ነው፡፡ በመሆኑም መንግሥታትና አጋሮችን በማሳመን የገቡትን ቃል እንዲያከብሩ፣ የሁለትዮሽ ስምምነት ካላቸው ኤጀንሲዎችና ከመንግሥታት ብሎም ከለጋሾች የሚገኘው ፈንድ እንዲቀጥል ለማድረግ ቅስቀሳ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ምንም እንኳ ጊዜው ገናም ቢሆን ስለዘላቂ የልማት ግቦችና ስለታዩት ስኬቶች ምን ሊባል ይችላል?

አቶ ሀዲስ፡- ስለዘላቂ የልማት ግቦች ብዙ ሊባል የሚችል ነገር አለ፡፡ ሪፖርቱም ይህንኑ ይጠቁማል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ያስመጥናቸው ግቦች የሚሳኩ ስለመሆናቸው ማወቅ ይኖርብናል፡፡ ይህም እንደሚሆን በዓለም የታየው የሚሌኒየሙ የልማት ግቦች ስኬት ማረጋገጫ ነው፡፡ ግቦቹን ለማሳካት የሚያስችለው መንገድ አሁን በሚገባ ግልጽ ሆኖ ተቀምጧል፡፡ ሪፖርቱም ይህንን አሳይቷል፡፡ የእኛ ሚና ያልተቋረጠ ቁርጠኝነት እንዲኖር ማድረግ፣ መንግሥታት የግቦቹ ባለቤት እንዲሆኑ ማድረግ፣ ኢንቨስትመንትና መሰል ግብዓቶችን በማካተት ግቦቹ እንዲሳኩ ማገዝ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ቅድሚያ በሚሰጣቸው ጉዳዮች ላይ ከማተኮር ይልቅ ወደ ሌሎች የማተኮር አዝማሚያ እየታየ ነው፡፡ ጦርነትና ሽብር፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የኢኮኖሚ መዝቀጥ፣ እንዲሁም የበጀት ቅነሳ እስካሁን ሲመዘገቡ የቆዩትን ውጤቶች ሥጋት ላይ እየጣሉ ነው፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ለዓለም አቀፍ ችግሮች መፍትሔ ሊሆኑ የሚችሉ ዘዴዎችን ከመፈለግ ሊያስቆሙን አይገባም፡፡ ከሪፖርቱ መውሰድ የሚቻለው አንድ ቁም ነገር የአፍሪካ መንግሥታት ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት የሚያስችሏቸው ጉዳዮች ላይ አመራር በመስጠት መቀጠል እንዳለባቸው ነው፡፡ ከዘላቂ የልማት ግቦች አኳያ ሪፖርቱ መሪዎች በየአገሮች የሚታዩ የልማት ችግሮችን ለመፍታት የተጠቀሙባቸውን ሥልቶች የሚያስቃኙ ታሪኮችንም አካቷል፡፡ ዓለም የዘላቂ የልማት ግቦችን እንድታሳካ ካስለፈገ፣ የታዳጊ አገሮችም ሆነ የለጋሽ አገሮች መሪዎች ያልተቋረጠ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ውስጥ ድሆች የአካታች ፋይናንስ ሥርዓት ተጠቃሚ መሆን ስለሚችሉባቸው መንገዶች እንነጋገር፡፡ ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ድሆችን ያካተተ የፋይናንስ አገልግሎት ማቅረብ ችላለች?

አቶ ሀዲስ፡- የኢትዮጵያን መደበኛው የፋይናንስ ሥርዓት (ባንኮችና የአነስተኛ የፋይናንስ ተቋማትን ጨምሮ) በተለያዩ ዘዴዎች በመታገዝ ቁጠባን የማሳደግ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ዲጂታል የፋይናንስ አገልግሎቶች ከተሞክሮ እንደታየውም የፋይናንስ ተደራሽነትን ብቻም ሳይሆን፣ የአገሪቱን የቁጠባ መጠን የማሳደግ ሚናም ሊጫወቱ ይችላሉ፡፡ ከማክሮ ኢኮኖሚ ዕይታ አንፃር የገንዘብ ዝውውር፣ የክፍያ፣ እንዲሁም የፍጆታ መጠንን መጨመር ብቻም ሳይሆን፣ በአሁኑ ወቅት ለኢትዮጵያ በጣም አስፈላጊው ጉዳይ የቁጠባ አቅምን ማሳደግ መቻል ነው፡፡ የዲጂታል ሥርዓት የቤተሰብ ቁጠባ ብሎም አገራዊ የቁጠባ መጠንን ለማሳደግ የሚያግዝ መሣሪያ መሆኑ እየታየ ነው፡፡ እየተስፋፋ የመጣው የሞባይል ስልክ ተጠቃሚዎች ቁጥር ልዩ አጋጣሚን ፈጥሯል፡፡ በየወሩ 1.5 ሚሊዮን ተጨማሪ ደንበኞችን በማፍራት ላይ የሚገኘው የአገሪቱ የሞባይል ስልክ ተጠቃሚዎች ቁጥር በአሁኑ ወቅት 50 በመቶ ደርሷል፡፡ ከአስምት ዓመት በፊት የሞባይል ስልክ ተመዝጋቢዎች ቁጥር ስድስት በመቶ ብቻ ነበር፡፡ በመሆኑም በገጠራማ አካባቢዎች ለሚኖረው ሕዝብ የፋይናንስ አቅርቦትን ለማዳረስ የሚያስችሉ ምቹ አጋጣሚዎች አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ቢልና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ የሞባይል ባንክ አገልግሎት መስክ ኢንቨስት እንደሚያደርግ ቢል ጌትስ አስታውቀው ነበር፡፡ ይህ ጉዳይ ከምን ደረሰ? ውጤቱስ ምንድነው?

አቶ ሀዲስ፡- ከሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ጋር በተጣጣመ ሁኔታ፣ የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ የሚያሳየውን ዕድገት ለማቀላጠፍ በአሳታፊ ፋይናንስ ረገድ በተለይም ለገጠሩ አካባቢ ተደራሽ እንዲሆን ለማድረግ ፋውንዴሽኑ ከመንግሥት ጋር እየተነጋገረ ነው፡፡ የመንግሥትን አሳታፊ የፋይናንስ ስትራቴጂዎች ለማገዝ የሚያስችሉ አጋጣሚዎቸ እንዳሉ እናስባለን፡፡ የተሟላ የፋይናንስ አቅርቦትና አካታችነት እንዲፈጠር የሚያግዝ ፍኖተ ካርታ ነው፡፡ የመንግሥት ክፍያዎችን በዲጂታል ሥርዓት ለማገዝ መንግሥት የሚያሳየው ቁርጠኝነትም አለ፡፡ መንግሥት በቅርቡ ‹‹Better than Cash Alliance›› የተባለውን ስምምነት ለመተግበር ተስማምቷል፡፡ የኅብረቱ አባላት አጋዥ ቡድን የመንግሥትን ክፍያዎች በዲጂታል ሥርዓት እንዲታገዙ ለማድረግ በአሁኑ ወቅት ስላለው አቅም ከመንግሥት ጋር በመሆን እየገመገመ ይገኛል፡፡ ክፍተቶችን ለመሙላት የሚያስፈልጉ ጉዳዮችንም ያያል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንደ ዲጂታል የክፍያ ዘዴ ያሉትን ጨምሮ፣ አሳታፊ የፋይናንስ ሥርዓት በመዘርጋት የፋይናንስ ተደራሽነትን ለማስፋት ያስቀመጠውን ግብ ለማሳካት የሚረዳው የቁጥጥር ሥርዓት መፍጠር እንዳለበት እናምናለን፡፡ በመሆኑም በክፍያ ሥርዓት ላይ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ እንዲቻል ከመንግሥት ጋር እየተነጋገርን እንገኛለን፡፡